የዩክሬን እና ሩሲያ ጦርነትን ለማስቆም የሚካሄደው ድርድር በመጪዎቹ ቀናት እንደሚጀመር ተነገረ
ድርድሩ በሳኡዲ አረብያ እንደሚካሄድ የአሜሪካ የመካከለኛው ምስራቅ ተወካይ አረጋግጠዋል

የአውሮፓ ሀገራት መሪዎች በበኩላቸው በትራምፕ ፖሊሲ እና በዩክሬን ጉዳይ በዛሬው ዕለት አስቸኳይ ስብሰባ ያደረጋሉ
በአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ከፍተኛ ትኩረት ከተሰጣቸው ጉዳዮች መካከል የዩክሬን እና ሩስያን ጦርነት የማስቆም ሂደት በመጪዎቹ ቀናት እንደሚጀመር ተሰምቷል፡፡
የትራምፕ የመካከለኛው ምስራቅ መልዕክተኛ ስቲቭ ዊትኮፍ የዩክሬንን ግጭት ለማስቆም በሚቀጥሉት ቀናት በሳኡዲ አረቢያ ውይይት እንደሚደረግ አረጋግጠዋል።
ዊትኮፍ በትላንትናው ዕለት ከአሜሪካ የብሔራዊ ደህንነት አማካሪ ማይክ ዋልትዝ ጋር በመሆን ወደ ሳኡዲ አረብያ አቅንተዋል፡፡
መልዕክተኛው ከፎክስ ኒውስ ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ ጦርነቱን ለማስቆም በሚደረገው ጥረት አንዳች ወሳኝ ነጥብ ላይ እንደሚደርሱ ገልጸው በሳኡዲ ከማን ጋር እንደሚገናኙ እና የውይይት ርዕሰ ጉዳዮችን ይፋ ከማድረግ ተቆጥበዋል፡፡
የአሜሪካ ከፍተኛ ባለስልጣናት በሚቀጥለው ሳምንት ከሩሲያ አቻዎቻቸው ጋር በሳኡዲ ዋና ከተማ ሪያድ የዩክሬን ግጭትን ለማስቆም ውይይቶችን ለመጀመር ቀጠሮ መያዛቸውን ዋሽንግተን ፖስት ስማቸው ያልተገለጸ የአሜሪካ ባለስልጣንን ጠቅሶ ዘግቧል።
በመጪዎቹ ቀናት እና በቀጣይ ሳምንት በሳኡዲ የሚካሄዱት ንግግሮች ከዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በሩሲያ እና በአሜሪካ ከፍተኛ ባለስልጣናት መካከል የሚካሄዱ ውይይቶች ናቸው፡፡
ቀደም ሲል የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮለድሚር ዘለንስኪ ኪየቭ በሳኡዲ አረቢያው ድርድር ላይ እንዳልተጋበዘች ተናግረው ነበር፡፡
ሆኖም የኢኮኖሚ ሚኒስትሯ ዩሊያ ስቪሪደንኮ በትላንትናው እለት የዩክሬን መንግስት የልዑካን ቡድን ወደ ሳኡዲ ማቅናቱን በፌስቡክ ገፃቸው አስታውቀዋል።
ሚኒስትሯ በመልዕክታቸው “በሚቀጥሉት ቀናት ኢኮኖሚያዊ ትስስርን ለማጠናከር፣ ከቀጠናው ሀገራት ጋር ስትራቴጂካዊ ስምምነቶችን ለመፈጸም እና የቮለድሚር ዘሌንስኪን የሳኡዲ አረቢያ ጉብኝት ለማመቻቸት የተለያዩ ውይይቶች ይካሄዳሉ” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በመጪዎቹ ቀናት በአሜሪካ ከፍተኛ ባለስልጣናት ከዩክሬን እና ከሩስያ ባለስልጣናት ጋር ያደርጉታል በተባለው ውይይት ማንም የአውሮፓ ሀገር እንዲሳተፍ ጥሪ አልደረሰውም፡፡
ይህን ተከትሎም የአውሮፓ መሪዎች በትራምፕ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ እና በአውሮፓ ላይ በሚኖረው ተጽዕኖ እንዲሁም በዩክሬን ጦርነት ዙሪያ ለመምከር በዛሬው ዕለት በፓሪስ አስቸኳይ ስብሰባ ለማድረግ ቀጠሮ ይዘዋል፡፡
ብሪታንያ እና ጀርመንን ጨምሮ ሌሎች የአውሮፓ ሀገራት የድርድር ሂደቱ በአውሮፓ ደህንነንት ላይ የሚያሳደርውን የደህንነት ስጋት ለመከላከል በዩክሬን የሰላም አስከባሪ ሀይል ለማሰማራት አቅደዋል፡፡
ከዚህ ባለፈም ሀገራቱ በኔቶ እና በተናጠል ወታደራዊ ወጪያቸውን ለማሳደግ ውይይት ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡