ሩሲያ “ምዕራቡን ዓለም በደቂቃዎች ሊያጠፋ ይችላል” በተባለ መሳሪያ ልምምድ እያደረገች ነው ተባለ
ታላላቅ የኒውከሌር ተሸካሚ አህጉር አቋራጭ ሀይፕርሶኒክ ሚሳዔሎችን ጫካ ውስጥ ስታጓጉዝ ታይቷል
“አር.ኤስ 28 ስማርት” ሚሳዔል 15 የኒኩሌር አረር የሚሸከም ሲሆን፤ በአንድ ጥቃት የብሪታኒያን ግማሽ ያክል ማውደም ይችላል
ሩሲያ የምእራቡን ዓለም በደቂቃዎች ማጥፋት በሚቻል ዙሪያ የኒኩሌር ሚሳዔል የጦር መሳሪያ ልምምድ እያደረገች ነው ሲል የብሪታኒያው ዘ ሰን ጋዜጣ አስነብቧል።
ጋዜጣው ባወጣው መረጃ ሩሲያ ታላላቅ አህጉር አቋራጭ ሀይፕርሶኒክ ሚሳዔል ማስወንጨፊያዎችን በኢቫኖቮ ክልል ውስጥ በሚገኝ ጫካ ውስጥ ስታጓጉዝ የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምስል መታየቱን አስታውቋል።
ልምምዱ የፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲንን ማስጠንቀቂያ ተከትሎ እየተካሄደ ነው የተባለ ሲሆን፤ ልምምድ አስምልከቶ የፕሬዝዳንቱ የቅርብ ሰው ዲሚትሪ ሮጎዚን በሰጡት አስተያየት ሩሲያ ካላት “ሳታን 2” ሚሳዔሎች ውስጥ 50 ያክሉን ልታሰማራ ነው ማለታቸው ተሰምቷል።
የሩሲያው ፕሬዝዳንት በምዕራቡ ዓለም ላይ በርካታ ዛቻዎችን የሰነዘሩ ሲሆን፤ ባለፈው ሳምንት ኒውክሌር ተሸካሚ ሚሳዔሎቻውን ሀገራቸው ከፊንላንድ ጋር ወደምትዋሰንባቸው ድንበሮች ማሰማራት መጀመሯም ተነግሯል።
ሩሲያ ሀገራት የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) መቀላቀል የሚያስከትላቸውን መዘዝ መሸከም አለባቸው ያለች ሲሆን፤ ሀገራው ከሰሞኑ ኔቶን ለመቀላቀል የጠየቀችውን ፊንላንድን በ “አስር ሰከንድ” ውስጥ ጠራርጎ የማጥፋት አቅም ያለው መሳሪያ እንዳላትም አስታውቀዋል።
የሩሲያ ስፔስ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ባሳለፍነው ሳምንት በሰጡት አስተያየት “ሳታን 2” የተባለው የሩሲያ ሚሳዔል የአሜሪካን ግምሽ ያክል ሊያወድም ይችላል ማለታቸው ይታወሳል።
“ሳታን 2” የተባለው የሩሲያ ሚሳዔል በቅርብ ጊዜ ውስጥ ወደ ስምሪት ሊገባ እንደሚችል መናገራቸውም ይታወሳል።
ሩሲያ የታጠቀቻቸው አውዳሚ የጦር መሳሪያዎች
ያሪሰረ ቴርሞኒኩሌር ሚሳዔል ሩሲያ ከታጠቀቻው ሚሳዔሎች ውስጥ አንዱ ሲሆን፤ 6 የኒኩሌር አረሮችን የሚሸከም እና በሰዓት 24 ሺህ ኪሎምትር በመፍጠን ኢላማዎችን መምታት የሚችል ነው።
አር.ኤስ 28 ስማርትም ሌላኛው የሩሲያ ሚሳዔል ሲሆን፤ ከባለ 14 ወለል ህንጻ ጋር እኩል ቁመት ያለውና 208 ቶን ክብደት የሚመዝነው ሚሳዔሉ በሰዓት እስከ 25 ሺህ ኪሎ ሜትር ይወነጨፋል ተብሏል።
ሚሳዔሉ በአንድ ጊዜ 15 የኒኩሌር አረር መሸከም ይችላል የተባለ ሲሆን፤ በአንድ ጥቃት ብቻ የብሪታኒያን ግማሽ ያክል ማውደም ይችላል ተብሏል።