ከአንድ ሺህ በላይ የዩክሬን ባህር ኃይል አባላት እጅ መስጠታቸውን ሩሲያ ገለጸች
ባህር ኃይል አባላቱ እጅ የሰጡት ከሩሲያ ወታደሮች ጋር በማሪዮፖል የወደብ ከተማ በተደረገ ውጊያ ነው
የሩሲያ ዩክሬን ጦርነት ከተጀመረ 50 ቀን ሆኖታል
ከአንድ ሺህ በላይ የዩክሬን ባህር ኃይል አባላት እጅ መስጠታቸውን ሩሲያ ገለጸች፡፡
ዩክሬን የሰሜን አትላንቲክ ቃልኪዳን ጦር ወይም ኔቶን እቀላቀላለሁ ማለቷን ተከትሎ ወደ ጦርነት የገቡት ሩሲያ እና ዩክሬን በሁለቱ አገራትን ጨምሮ በዓለም የዕለት ተዕለት ሁኔታ ላይ ተጽዕኖ አሳርፏል፡፡
50 ቀኑ ላይ በሚገኘው በዚህ ጦርነት እስካሁን ከ5 ሚሊዮን በላይ ዩክሬናዊያን አገራቸውን ለቀው ወደ ጎረቤት አገራት የተሰደዱ ሲሆን በርካቶች ደግሞ ህይወታቸውን፣አካላቸውን እና ንብረታቸውን አጥተዋል፡፡
የዩክሬን የወደብ ከተማ በሆነችው ማሪዮፖል በተካሄደው ጦርነት ከ1 ሺህ በላይ የዩክሬን ባህር ኃይል አባላት ለሩሲያ ጦር እጅ መስጠታቸውን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
የጦሩ ቃል አቀባይ ሜ/ጄ ኢጎር ካኒሼንኮቭ 1026 የዩክሬን ባህር ኃይል 36ኛ ብርጌድ አባላት እጅ መስጠታቸውን ተናግረዋል፡፡
ከ1026ቱ ውስጥ 162 መኮንኖች እና 47ቱ ሴት የብርጌዱን ሰራተኞች ያካተተ ነው፡፡ 151 የቆሰሉ ሲሆን ህክምና አግኝተዋል ብለዋል ቃል አቀባዩ።
የሩሲያ ጦር ካሳለፍነው የካቲት ወር ጀምሮ የወደብ ከተማዋን ከቦ ይገኛል፡፡ ይህም በከተማዋ ይገኙ የነበሩ የዩክሬን ወታደራዊ አሃዶች ምግብን ጨምሮ ለተለያዩ ወታደራዊ ግብዓቶች እጥረት እንዲዳረጉ ምክንያት ሆኗል፡፡
የዩክሬን ፕሬዝዳንት በአፍሪካ ህብረት ንግግር ለማድረግ ጠየቁ
የሩሲያዋ ቺቺኒያ መሪ ራምዛን ካዲሮቭ በቴሌግራም ገጻቸው ያሰፈሩትን መግለጫ ዋቢ አድርጎ ሮይተርስ እንደዘገበው የዩክሬን ባህር ሀይል ወታደሮች አጅ በመስጠት ላይ መሆናቸውን ተናግረው ቀሪ ወታደሮችም እጅ እንዲሰጡ አስጠንቅቀዋል፡፡
ይሁንና እስካሁን እጅ ስለሰጡት የዩክሬን ወታደሮች በዩክሬን ባለስልጣን በኩል የተባለ ነገር የለም፡፡
የዩክሬን መንግስት ዛሬ ጠዋት ባወጣው መግለጫ የሩሲያ ጦር በምስራቃዊ የሃገሪቱ ክፍል በአዛቭስታለ ወደብ በኩል አዲስ ጥቃት መጀመሩን አስታውቋል፡፡
የሩሲያ መከላከያ በበኩሉ የዩክሬን ወታደሮች እጅ መስጠታቸውን እንዲቀጥሉ እና የጀመሩትን ውጊያ በማቆም ወደ ቤተሰቦቻቸው እንዲቀላቀሉ አሳስቧል፡፡
የሩሲያ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ደጋፊ እንደሆኑ የሚነገርላቸው የቺቺኒያው መሪ ካዲሮቭ የዩክሬኗን ዋነኛ የወደብ ከተማ ማሪዮፖል መቆጣጠሩን ገልጾ በጥቂት ቀናት ውስጥ ሁሉንም ከተሞች እንደሚቆጣጠሩ ተናግረዋል፡፡