የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር፣ የሩሲያ አየር ኃይል የዩክሬን ጦር ያስወነጨፋቸውን 10 የረጅም ርቀት ሚሳይሎች ማክሸፉን አስታውቋል
ሩሲያ ወደ ክሪሚያ የተወነጨፉ 10 ሚሳይሎችን አከሸፍኩ አለች።
የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር፣ የሩሲያ አየር ኃይል የዩክሬን ጦር ወደ ክሪሚያ ያስወነጨፋቸውን 10 ኤቲኤሲኤምኤስ የተባሉ የረጅም ርቀት ሚሳይሎች በዛሬው እለት ማክሸፉን አስታውቋል።
ሚኒስቴሩ በቴሌግራም ገጹ ባወጣው መግለጫ በተወነጨፉት ሚሳይሎች የደረሰ ጉዳት ስለመኖሩ አልጠቀሰም፤ ነገርግን በሩሲያ የተሾሙት የክሪሚያዋ የወደብ ከተማ ሴቫስቶፖል አስተዳደሪ የሚሳይሎቹ ስብርባሪ መኖሪያ ቤቶች ላይ መውደቃቸውን ተናግረዋል።
አስተዳዳሪው ሚካኤል ሮዝቮዛይቭ በቅድመ ምርመራ ውጤቱ መሰረት ጉዳት የደረሰበት ሰው የለም ሲሉ በቴሌግራም ገጻቸው ገልጸዋል።
ሩሲያ ክሪሚያን ወደ ግዛቷ የጠቀለለችው ከ10 አመት በፊት ነበር። በወቅቱ ሩሲያ በዩክሬን እና በምዕራባውያን ላይ ከፍተኛ ተቃውሞ ደርሶባት ነበር።
ሩሲያ ተጨባጭ ምክንያት ባታቀርብም ዩክሬን አሜሪካ ያቀረበችላትን አርሚ ታክቲካል ሚሳይል ሲስተም ወይም ኤቲኤሲኤምኤስን እየተጠቀመች ነው ብላለች።
የአሜሪካ ባለስልጣን ባለፈው ሚያዝያ ወር በፕሬዝደንት ጆ ባይደን የጸደቀው ኤቲኤሲኤምኤስ እና የአየር ጥቃት መቃወሚያ በዩክሬን እጅ መግባታቸውን ገልጸዋል።
የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር አክሎም ዘጠኝ ድሮኖች እና ሌሎች ዩክሬን የተኮሰቻቸውን መሳሪያዎች በቤልጎርድ ግዛት መክሸፋቸውን ገልጿል።
የአሜሪካ ተወካዮች ምክርቤት ባለፈው ወር ከሩሲያ ጋር እየተዋጋች ላለችው ዩክሬን እና ለሌሎች የአሜሪካ አጋሮች የሚለውል የ95 ቢሊዮን ወታደራዊ እርዳታ አጽድቋል። ከጸደቀው ወታደራዊ እርዳታ ውስጥ 61 ቢሊዮን ዶላሩ የተሰጠው ለዩክሬን ነው።
ዩክሬን አሜሪካ የለገሰቻት የጦር መሳሪያ በምሰራቅ ዩክሬን ጥቃት የከፈተችባትን ሩሲያን ለመመከት ያስችላታል ተብሏል።
በምስራቅ ዩክሬን አብዲቪካን ጨምሮ በርካታ መንደሮችን የተቆጣጠረችው ሩሲያ፣ በቅርቡ በሰሜን ምሰራቅ ዩክሬን አምስት መንደሮችን መቆጣጠሯን አስታውቃለች።
ሩሲያ በሰሜን ምስራቅ ዩክሬን ጥቃት የከፈተችው በድንበር ያሉ ግዛቶቿን ከባድ መሳሪያ የማይደርስበትን ርቀት ለመፍጠር አስባ መሆኑን ገልጻለች።