የሩሲያ ጦር ከ 50 በላይ የዩክሬን ወታደራዊ ኢላማዎችን “መታሁ” አለ
ሩሲያ እስካሁን 125 የጦር አውሮፕላኖችንና ሌሎች መሳሪያዎችን ማውደሟን አስታውቃለች
ሩሲያ 88 ሄሊኮፍተሮችም ከጥቅም ውጭ አድርጋለች ተብሏል
የሩሲያ ጦር በዩክሬን ወታደራዊ ኢላማዎች ላይ ጥቃት መሰንዘሩን የሀገሪቱ መከላከያ መስሪያ ቤት አስታወቀ፡፡
የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ኢጎር ኮናሸንኮቭ ዛሬ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ የሀገራቸው ጦር 51 ወታደራዊ ኢላማዎች ላይ ጥቃት መሰንዘሩን ገልጸዋል፡፡ ጦሩ በሁለት የከባድ መሳሪያ ክላስተር እና ብዙ በሚተፋ ተወንጫፊ ሮኬት ሲስተም ላይ የተሳካ ጥቃት ማድረሱ ተገልጿል፡፡
ኢላማዎቹን የመታው የሩሲያ የኤሮስፔስ ኃይል መሆኑን የገለጹት ቃል አቀባዩ በዩክሬን ወታደራዊ መሳሪያዎች ላይ ኪሳራ ደርሷልም ብለዋል፡፡ የሩሲያ ጦር በባሕር እና በአየር ጥቃት በመታገዝ በፈጸመው ጥቃት የዘይት ማጣሪያ እንዲሁም ሶስት የነዳጅ ዲፖዎችን አጥቅቷል ብለዋል፡፡
ጥቃት የተፈጸመባቸው ዲፖዎች ለዩክሬን ወታደሮች ነዳጅ የሚቀርብባቸውና የሚቀዳባቸው መሆናቸውን የሩሲያ መንግስት ዜና አገልግሎት ታስ ዘግቧል፡፡ በዚህም መሰረት የነዳጅና የዘይት ዲፖዎቹ ሙሉ ለሙሉ ተወግደዋል ነው የተባለው፡፡
ሩሲያ በዩክሬን “ወታደራዊ ዘመቻ” ከጀመረችበት ዕለት ጀምሮ እስካሁን ጦሯ 125 የጦር አውሮፕላኖች፣ 88 ሂሊኮፍተሮች፣ 383 ድሮኖች ከጥቅም ውጭ ማድረጉን የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አስታውቀዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ሩሲያ 1 ሺ 903 ታንኮችን፣ 207 ተወንጫፊ ሮኬቶችን፣ 1 ሺ 781 ልዩ ወታደራዊ ተሽከርካሪዎችን፣ 221 ሚሳኤሎችን፣ 805 የመስክ ከባድ መሳሪያዎችና ሞርታሮችን ከጥቅም ውጭ አድርጋለች ተብሏል፡፡
ዛሬም የዩክሬን ኤሮስፔስ ሁለት ድሮኖችን መቶ መጣሉ ተገልጿል፡፡ሩሲያ እና ዩክሬን አሁንም ውጊያ ላይ ቢሆኑም ድርድር በማድረግ ላይ ናቸው፡፡