ሩስያ የዩክሬንን ድሮን መጣሏን ገለጸች
የሩስያን ድንበር አልፋ የገባችው ድሮን ስብርባሪም ሶስት የሩስያ አየር ሃይል አባላትን መግደሉን ነው ሞስኮ ያስታወቀችው

በዩክሬን ድንበር ላይ የሚገኘው የሩስያ ኤንጂልስ አየር ጣቢያ ላይ ሊፈጸም ነበር ስለተባለው የድሮን ጥቃት ዩክሬን ምላሽ አልሰጠችም
ሩስያ ድንበሯን ጥሳ የገባች የዩክሬን ድሮን መጣሏን ገለጸች።
በዩክሬን ድንበር ላይ በሚገኘው የሩስያ ኤንጂልስ አየር ጣቢያ ላይ ያነጣጠረ ጥቃት ልትፍጽም ነበር የተባለችው ድሮንን ተሰባብራ ስትወድቅም ሶስት የሩስያ አየር ሃይል አባላት ህይወታቸው ማለፉን ነው የሩስያ መከላከያ ሚኒስቴር ያስታወቀው።
ከወር በፊት በርካታ ቦምብ ጣይ አውሮፕላኖች ተከማችተውበት የነበረው የአየር ጣቢያ ላይ ግን የደረሰ ጉዳት የለም ብሏል ሚኒስቴሩ።
- በዩክሬን ድንበር የተደረደሩ የሩስያ የጦር አውሮፕላኖች ምን እየተጠባበቁ ነው?
- የዩክሬን ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ “የሩስያ አውዳሚ ጦርነት የሚያበቃበት ጊዜ አሁን ነው” አሉ
ከዩክሬን የማህበራዊ ትስስር ገጾች የሚወጡ ያልተረጋገጡ መረጃዎች ግን የሩስያ አውሮፕላኖች ስለመመታታቸው ያመላክታሉ።
ሬውተርስ በበኩሉ መርጃዎቹን ማረጋገጥ እንዳልቻለ ነው የዘገበው።
የኤግልስ አየር ጣቢያ ከዩክሬን ድንበር ከ600 በላይ ኪሎሜትሮች ርቆ የሚገኝ ሲሆን ቲዩ 95 እና ቲዩ 160 የተሰኙ ኒዩክሌር ቦምብ ተሸካሚ የጦር አውሮፕላኖች ተከማችተውበታል።
ሞስኮ በኬቭ ከተሞች ላይ የአየር ላይ ጥቃት የምትፈጽመውም ከዚሁ ጣቢያ እየተነሳች መሆኑ ይነገራል።
በዛሬው እለት የኬቭ ድሮን በመቶ ኪሎሜትሮች ዘልቃ ገብታ ይህን ጣቢያ ለማጥቃት መሞከሯ የሞስኮን የአየር መቃወሚያ ስርአት ጥያቄ ውስጥ ከቶታል።
ከዩክሬን በኩል ስለጥቃት ሙከራው እስካሁን የተሰጠ ምላሽ የለም።
ባለፈው ወርም በሳቫሮቭ ግዛት በሚገኘው የአየር ጣቢያ በዩክሬን ድሮኖች የጥቃት ሙከራ አስተናግዶ እንደነበር የሚታወስ ነው።