ክሬሚሊን ሾልኮ የወጣው የድምጽ ቅጂ ጀርመን ሩሲያን የመምታት እቅድ እንዳላት የሚያሳይ ነው አለ
ሾልኮ ወጥቷል ባሉት የድምጽ ቅጅ፣ የጀርመን ወታደራዊ መኮንኖች ለዩክሬን የጦር መሳሪያ ድጋፍ ስለማድረግ እና ኪቭ የክሪሚያ ድልድይን ስለምትመታበት ሁኔታ ውይይት አድርገዋል
ክሬሚሊን፣ ሩሲያ በውይይቱ የጀርመን መራሄ መንግሰት ኦላፍ ሽሎዝ ተሳትፎን ስለመኖሩ ማወቅ እንደምትፈልግ ገልጿል
ክሬሚሊን ሾልኮ የወጣው የድምጽ ቅጂ ጀርመን ሩሲያን የመምታት እቅድ እንዳላት የሚያሳይ ነው አለ።
የሩሲያ ቤተ መንግስት ጽ/ቤት ክሬሚሊን በዛሬው እለት እንደገለጸው ሾልኮ የወጣው የጀርመን ወታደራዊ መኮንኖች ውይይት፣ የጀርመን ጦር በሩሲያ ላይ ጥቃት በመሰንዘር እቅድ ላይ መወያየቱን የሚያሳይ መሆኑን በዛሬው እለት ገልጿል።
ክሬሚሊን፣ ሩሲያ በውይይቱ የጀርመን መራሄ መንግሰት ኦላፍ ሽሎዝ ተሳትፎን ስለመኖሩ ማወቅ እንደምትፈልግ ገልጿል።
ባለፈው ሳምንት የሩሲያ ሚዲያዎች ሾልኮ ወጥቷል ባሉት የድምጽ ቅጅ፣ የጀርመን ወታደራዊ መኮንኖች ለዩክሬን የጦር መሳሪያ ድጋፍ ስለማድረግ እና ኪቭ የክሪሚያ ድልድይን ስለምትመታበት ሁኔታ ውይይት አድርገዋል።
ይህ ጉዳይ ሩሲያ ተጨማሪ ማብራሪያ እንድትጠይቅ አስገድዷታል።
"የድምጽ ቅጅው በራሱ በሩሲያ ግዛት ውስጥ ጥቃት ለማድረስ በሚያስችል እቅድ ላይ ውይይት መደረጉን ያሳያል። ይህ ሌላ የህግ ትርጓሜ የሚሰጠው አይደለም። እዚህ ያለው ነገር ግልጽ ነው።" ሲሉ የክሬሚሊን ቃል አቀባይ ዲሜትሪ ፔስኮቭ ተናግረዋል።
ፔስኮቮ "እዚሀ ላይ ማወቅ የምንፈልገው ወታራዊ መኮንኖቹ ይህን እየሰሩ ያሉት በራሳቸው ተነሳሽነት ነው ወይ የሚለውን ነው። ጥያቄው ኦላፍ ሽሎዝ ሁኔታውን ምን ያህል ይቆጣጠረው ነበር የሚለው ነው?፤ ወይስ የጀርመን ፖሊሲ ነው?" ሲሉ ይጠይቃሉ።
ፔስኮቭ እንደተናገሩት "ሁለቱም ቢሆኖች በጣም መጥፎዎች ናቸው"ብለዋል።
ፔስኮብ ምዕራባውን በዩክሬን እየተካሄደ ባለው ጦርነት በቀጥታ የሚሳተፉ ከሆነ አደጋው የከፋ እንደሚሆን ተናግረዋል።
ጀርመን ወጣ የተባለውን መረጃ እንደምትመረምረው መግለጿ ይታወሳል።
ጀርመን ለዩክሬን የጦር መሳሪያ ከሚያቀርቡ የኔቶ አባል ሀገራት አንዷ ነች።
ሩሲያ ምዕራባውያን በትብብር ዩክሬንን ተጠቅመው የውክለና ጦርነት እንደከፈቱባት ስትከስ፣ ምዕራባውያን ግን ዩክሬንን የሚረዱት ራሷን እንድትከላከል ነው በማለት ክሱን አይቀበሉትም።
ሩሲያ በዛሬው እለት በሞስኮ የጀርመን አምባሳደርን በሚስጥራዊ ውይይቱ ጉዳይ ማብራሪያ ለመጠየቅ ጠርታለች።
የፈረንሳይ ፕሬዝደንት ኢማኑኤል ማክሮን ባለፈው ሳምንት የአውሮፖ ሀገራት ወደ ዩክሬን ጦር ሊልኩ ይችላሉ ማለታቸውን ተከትሎ የሩሲያው ፕሬዝደንት ፑቲን የፈረንሳይ ወታደሮች በ1812 ሩሲያን እንደወረሩት የናፖሊዮን ወታደሮች ሽንፈት ይከናነባሉ የሚል መልስ መስጠታቸው ይታወሳል።