የአሜሪካ ፕሬዝደንት ጆ ባይደን ፑቲን ስልጣን ላይ መቆየት የለባቸውም ማለታቸው በሩሲያ ቁጣን ቀስቅሷል
ሩሲያ እንደሀገር የመቀጠል ህልውናዋ አደጋ ላይ ከወደቀ የኑክለር ጦር መሳሪያ ልትጠቅም እንደምትችለ ገልጻለች፡፡
የአሜሪካ ፕሬዝደንት ጆ ባይደን ስለ ሩሲያ ፕሬዝደንት ፑቲን በሰጡት አስተያያት ላይ ምላሽ የሰጡት የሩሲያ ቤተመንግስት ቃል አቀባይ ስለኑክለር አስተያየት ሰጥተዋል፡፡
ቃል አቀባዩ ዲሜትሪ ፓስኮቭ ከአሜሪካው ፒቢኤስ ጋር በደረጉት ቆይታ ሩሲያ ህልውናዋን አደጋ ውስጥ የሚከት ስጋት ካጋጠማት ብቻ የኑክለር ጦር መሳሪያ ልትጠቀም እንደምትችል ተናግረዋል፡፡
የአሜሪካው ፕሬዝደንት ጆ ባይደን ስለ ፑቲን ስልጣን መቆየት የሰጡት አስተያየት የሚረብሽ እና ግለሰብ ላይ ያነጣጠረ ስድብ ነው ያሉት ቃል አቀባዩ ኔቶ የመፋጠጫ ማሽን ነው ብለዋል፡፡
“በዩክሬን ውስጥ በምናደርገው ዘመቻ የኑክለር ጦር መሳሪያ የምንጠቀምበት ምክንያት የለም፣…እኛ ባለን ግልጽ ፖሊሲ ላይ እንደተቀመጠው የኑክለር ጦር መሳሪያ የምንጠቀም እንደሀገር መቀጠላችን አደጋ ከተጋረጠት ብቻ ነው፣ ስጋቱን ለማጥፋት ኑክለር እንጠቀማን” ብለዋል፡፡
የአሜሪካው ፕሬዝደንት ጆ ባይደን ፑቲን ስልጣን ላይ መቆየት የለባቸውም ማለታቸው፣ ፕሬዝዳንቱ ሩሲያ በምታካሂደው ወታደራዊ ዘመቻ ምን ያህል መናደዳቸውን የሚያሳይ ነው ተብሏል፡፡
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ስልጣን ላይ መቆየት እንደማይችሉ መናገራቸው የግል አስተያየት እንጂ የሃገራቸው አቋም እንዳልሆነ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ተናግረዋል፡፡
ባይደን ከንግግሩ ጋር በተያያዘ እንዲያብራሩ እና የፖሊሲ ለውጥ ስለመኖሩ እንዲናገሩ በጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ በምላሹ በአሜሪካ በኩል በሩሲያ የአገዛዝ ለውጥ እንዲደረግ ፍላጎት እንደሌለ ገልጸዋል፡፡