አሜሪካ የቻይናን ግንኙነት የማቋረጥ ድርጊት አውግዛ ነበር
ሩሲያ ከአሜሪካ ጋር ያላትን ሁሉን አቀፍ ትብብር ልታቋርጥ እንደምትችል አስጠነቀቀች፡፡
የሩሲያ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ሀገሪቱ ከአሜሪካ ጋር ያላትን ማንኛውም ግንኙነት ልታቋርጥ እንደምትችል አስታውቋል፡፡ በሩሲያ እና ዩክሬን መካከል ባለው ጦርነት አሜሪካ ዋነኛዋ ተዋናይ መሆኗን ሞስኮ ገልጻለች፡፡
ሩሲያ ይህንን ማስጠንቀቂያ የሰጠችው አሜሪካ የሩሲያን ሀብቶች ለመያዝ ዕቅድ ማዘጋጀቷን ተከትሎ መሆኑን የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ገልጿል፡፡
አሜሪካ፤ የሩሲያን ሀብት ለመያዝ ያዘጋጀችውን ሰነድ ተግባራዊ እንዳታደርገው ሞስኮ እያስጠነቀቀች ነው፡፡ በሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ምክንያት ከሩሲያ ጋር ግጭት ውስጥ የገባችው አሜሪካ በታይዋን ጉዳይም ከቻይና ጋር አታካራ ውስጥ ገብታለች፡፡
የአሜሪካ ምክር ቤት አፈጉባዔ ናንሲ ፔሎሲ፤ ታይዋንን መጎብኘታቸውን ተከትሎ ቤጅንግ እና ዋሸንግተን የቃላት ጦርነት ውስጥ ገብተዋል፡፡ ከዚህ ባለፈም ቻይና በፔሎሲ እና በቤተሰቦቻቸው ላይ ማዕቀብ ከመጣልም አልፎ በአሜሪካ ላይ እርምጃ መውሰዷን ገልጻለች፡፡
በዚህ የተነሳም ቻይና ከአሜሪካ ጋር የነበራትን ወታደራዊ ትብብር ማቋረጧን አስታውቃለች። አሁን ላይ አሜሪካ በኢኮኖሚ እና በወታደራዊ ጉዳዮች ላይ ከሚፎካከሯት ቻይና እና ሩሲያ ጋር በተመሳሳይ ጊዜ እሰጥ አገባ ውስጥ ገብታለች፡፡
የናንሲ ፔሎሲ ጉብኝት እና የዩክሬን ጦርነት አሜሪካ፤ ከሩሲያ እና ቻይና ጋር ያላትን ግንኙነት የሚወስኑ ጉዳዮች መስለዋል፡፡ ቻይና ከፔሎሲ ጉብኝት በኋላ በታይዋን ስድስት አቅጣጫ የአየር፣ ባህር እና ሌሎች አይነት ወታደራዊ ልምምድ አድርጋለች፡፡
አሁን ደግሞ ቻይና ከአሜሪካ ጋር ያላትን ወታደራዊ ትብብሮችን ማቋረጧን ያሳወቀች ሲሆን ተጨማሪ ውሳኔዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ ሮይተርስ ዘግቧል።
አሜሪካ፣ በበከሏ ቻይና ከአሜሪካ ጋር ያላትን ወታደራዊ ትብብር ማቋረጧ ትክክል እንዳልሆነ ገልጻለች፡፡