ሩሲያ በኦዴሳ በፈጸመችው ጥቃት ምዕራባውያን ለዩክሬን የለገሱትን የጦር መሳሪያዎች ማውደሟን ገለፀች
ሩሲያ “የሚሳዔል ጥቃቱ ከዩክሬን አጋሮች ጩኸት ቀስቅሷል” ብላለች
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ዜለንስኪ በኦዴሳ ወደብ ላይ የተፈጸመው ጥቃት “አረመኔያዊ” ነው ሲሉ ገልጸውታል
ሩሲያ ወሳኝ የጥራጥሬ ምርት የመላክ ስምምነት ማእከል በሆነው የዩክሬን ኦዴሳ ወደብ ላይ የሰነዘረችው ጥቃት የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ያስደነገጠ መሆኑ ይታወቃል።
ጥቃቱ ምናልባትም በሩሲያ እና ዩክሬን መካከል የተደረሰው የእህል ምርትን ወደ ውጭ የመላክ ስምምነት የሚያፈርስ እንዳይሆንም ጭምር ተሰግቷል።
ጥቃቱ የተፈጸመው በሀገራቱ መካከል ታሪካዊ ስምምነት ከተደረሰ ከሰዓታት በኋላ እንደመሆኑ፤ በበርካቶች ዘንድ ስምምነቱ ላይሳካ ይችላል የሚል ስጋት እንዲፈጠር ምክንያት እንደሆነም ነው ኤኤፍፒ የዘገበው።
- ሩሲያ በኦዴሳ ወደብ ጥቃት መሰንዘሯ ጥራጥሬ የመላክ የስምምንት ላይ "ከባድ ጥርጣሬ" የሚፈጥር ነው ተባለ
- ሩሲያ አሜሪካ ለዩክሬን የሰጠችውን የረጅም ርቀት ሮኬት ስርዓት አወደምኩ አለች
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ዜለንሰኪ ጥቃቱን ሞስኮ ስምምነቱን ስለማክበሯ እንደማትታመን የሚያሳይ መሆኑ ተናግረዋል። ሩሲያ በኦዴሳ ወደብ ላይ ያደረሰችውን ጥቃት “አረመኔያዊ” ነውም ነበር ያሉት ፕሬዝዳንቱ።
ጥቃቱን ከዩክሬን በተጨማሪ በርካቶች ያወገዙት ሲሆን፤ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ሩሲያ የዓለም የምግብ ቀውስን እያባባሰች ነው ሲሉ በትዊተር ገጻቸው ባጋሩት ጽሁፍ ከሰዋል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝም እንዲሁ ጥቃቱን ያወገዙ ሲሆን “የእህል ስምምነቱን ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ማድረግ አስፈላጊ ነው” ሲሉ ስምምነቱ እንዳይስተጓገል ስጋታቸው ገልጸዋል።
ዘግይታም ቢሆን በጉዳዩ ላይ ምላሽ የሰጠችው ሩሲያ ጥቃቱ ዩክሬን እና አጋሮቿ እንደሚሉት ሳይሆን ምዕራባውያን ያቀረቧቸውን የጦር መሳሪያዎች ያወደመ ነበር ብላለች።
የሩስያ መከላከያ ሚኒስቴር በሰጠው መግለጫ “በጥቃቱ ዋሽንግተን ያስረከበችውን የዩክሬን ወታደራዊ መርከብ እና የጦር መሳሪያ ወድሟል” በዚህም የዩክሬን ጦር መሳሪያ ጥገና እና ማሻሻያ ፋብሪካ ከአገልግሎት ውጭ ሆኗል ብሏል።
በተጨማሪም “ጥቃቱ ከዩክሬን አጋሮች ጩኸት ቀስቅሷል”ም ሲል አክሏል የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር በመግለጫው።