ሩሲያ በሌሎች ሀገራት ፍላጎቷን ለማስጠበቅ 300 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ማድረጓን አሜሪካ ገለጸች
ሩሲያ በአምስት አህጉራት ለሚገኙ ከ20 በላይ ሀገራት ገንዘብ ፈሰስ አድርጋለች ተብሏል
ሩሲያ እስካሁን በአሜሪካ ክስ ዙሪያ ምላሽ አልሰጠችም
ሩሲያ በሌሎች ሀገራት ፍላጎቷን ለማስጠበቅ 300 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ማድረጓን አሜሪካ ገለጸች።
የአሜሪካ የደህንነት ተቋም ባወጣው መረጃ ሩሲያ በተለያዩ የዓለማችን ሀገራት የፖለቲካ ፍላጎቷን ያስፈጽሙልኛል ያለቻቸውን እጩዎች እና ፓርቲዎች በገንዘብ እየረዳች ነው ብሏል።
እንደ ሮይተርስ ዘገባ ከሆነ ሩሲያ በአምስት አህጉራት ለሚገኙ ከ20 በላይ ሀገራት ከ300 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገንዘብ ፈሰስ አድርጋለች ።
በተለይም ከፈረንጆቹ 2014 ጀምሮ ለአውሮፓ፣ እስያ፣ አፍሪካ እና ሁለቱ የአሜሪካ አህጉራት ስር ላሉ ሀገራት በተለያየ መንገድ ገንዘብ ሰጥታለች ተብሏል።
ሩሲያ ገንዘቡን ፈሰስ የምታደርገው በፋውንዴሽን ስም በተቋቀቋሙ ድርጅቶች እና ለይስሙላ በተቋቋሙ የንግድ ድርጅቶች ስም እንደሆነም አሜሪካ ገልጻለች።
አሜሪካ በሩሲያ የገንዘብ ድጋፍ የተደረገላቸውን ሀገራት ለጊዜው ያልጠቀሰች ሲሆን ከአውሮፓ አልባኒያ፣ ቦስኒያ እና ሄርዜጎቪና፣ ሞንቴኔግሮ ሲሆኑ ከአፍሪካ ደግሞ ሜዳጋስካር አንዷ መሆኗን ኤኤፍፒ ከፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ጽህፈት ቤት ያገኘውን መረጃ ዋቢ አድርጎ ዘግቧል።
ሩሲያ ገንዘቡን ወደ ምትፈልጋቸው ሀገራት እና የፓርቲ እጩዎች ቤልጂየም እና ኢኳዶር ከሚገኙት የሩሲያ ኢምባሲዎች በኩል እንደሆነም ተጠቅሷል።
አሜሪካም የፓለቲካ ፍላጎቶቿን ለማስፈጸም በተለያዩ የዓለማችን ሀገራት ላይ በሲአይኤ በኩል ጣልቃ በመግባት መፈንቅለ መንግስት እስከማስፈጸም የሚደርስ ሙከራ ታደርጋለች የሚል ክስ እንደሚነሳባት የጀርመን ድምጽ ዘግቧል።
በተለይም በኢራን እና በቺሊ ሲአይኤ መፈንቅለ መንግስት እንዲፈጸም አድርጓል በሚል የሚቀርብባትን ክስ አሜሪካ ውድቅ አድርጋለችም ተብሏል።
የፕሬዝዳንት ጆ ባይደን አስተዳድር በሩሲያ ላይ ያቀረበውን ክስ ራሷ አሜሪካ በዲሞክራሲ እና መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች ስም ትፈጽማለች በሚል የቀረበበትን ክስ ውድቅ ማድረጉም ተገልጿል።ሩሲያ በአሜሪካ በቀረበባት ክስ ዙሪያ እስካሁን ምላሽ እንዳልሰጠች ተገልጿል።