የፕሬዝዳንት ፑቲን ሁለት ሴት ልጆች ማን ናቸው፤ በምን ስራ ተሰማርተዋል?
አሜሪካ በሩሲያው ፕሬዝዳንት ፑቲን ሁለት ልጆች ላይ ማዕቀብ መጣሏ ተሰምቷል።
ማዕቀቡ የሩሲያ ፕሬዝዳንት ሁለት ሴት ልጆች የሆኑት ካትሪና እና ማሪያ ላይ መጣሉን አሜሪካ አስታውቃለች።
አሜሪካ በፕሬዝዳንቱ ልጆች ላይ ማዕቀቡን የጣለችው ፕሬዝዳንቱ ንብረቱን በልጆቹ በኩል ሊያሸሽ ይችላል በሚል ስጋት እንደሆነ ሮይተርስ ዘግቧል።
ካትሪናና ማሪያ የተባሉት የፕሬዝዳንት ፑቲን ሁለት ሴት ልጆች ማን ናቸው ?
እንደ ከሬምሊን ድረ ገጽ መረጃ ከሆነ የፕሬዝደንት ፑቲን የመጀመሪያ ሴት ልጅ የሆነችው ማሪያ በፈረንጆቹ 1985 የተወለደች ሲሆን፤ ሁለተኛዋ ልጅ ካትሪና ደግሞ ከዓመት በኋላ በ1986 ነው የተወለደችው።
ሁለቱ ልጆች ቭላድሚር ፑቲን በምስራቅ ጀርመን የሩሲያው የደህንነት ተቋም ኬጂቢ ሰላይ በነበሩበት ወቅት መወለዳቸውም መረጃዎች ይጠቁማሉ።
የፕሬዝዳንት ፑቲን የመጀመሪያ ሴት ልጅ የሆነችው የ35 ዓመቷ ካትሪና፤ የቴክኖሎጂ ቡድን ስራ አስኪያጅ ስትሆን የሩሲያ መንግስትን እና መከላከያን እንደምታግዝ ተገልጿል።
ሌላኛዋ የፕሬዘዳንቱ ሴት ልጅ የሆነችው ማሪያ ደግሞ በሩሲያ መንግስት የሚደገፍ የዘረ መል ልማት ድርጅትን በመምራት ላይ ትገኛለች ተብሏል።
አሜሪካ ማዕቀቡን ከፕሬዝደንት ፑቲን ልጆች በተጨማሪም በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሰርጊ ላቭሮቭ ሚስት እና ሴት ልጃቸው ላይም ማዕቀብ መጣሏን አስታውቃለች።
ሩሲያ በዩክሬን ላይ አካሄድኩት ባለችው ልዩ ዘመቻ ንጹሃንን ኢላማ ያደረጉ ግድያዎች እና ሌሎች ጉዳቶችን አድርሳለች በሚል በመዕራባዊያን በመከሰስ ላይ ብትሆንም ሩሲያ ግን ድርጊቱን እንዳልፈጸመች አስታውቃለች።
ዩክሬን የሰሜን አትላንቲክ ቃልኪዳን ጦር ኔቶን እቀላቀላለሁ ማለቷን ተከትሎ ከሩሲያ ጋር ወደ ጦርነት ማምራታቸው ይታወሳል።
ይህ ጦርነት ከአራት ሚሊዮን በላይ ዩክሬናዊያን ወደ ጎረቤት ሀገራት እንዲሰደዱ ሲያደርግ በርካቶች እንዲሞቱ እና ንብረት እንዲወድም ምክንያት ሆኗል።
ሩሲያ ዩክሬንን በመውረሯ አሜሪካንን ጨምሮ በረካታ የዓለማችን ሀገራት በሩሲያ ላይ ማዕቀቦችን በመጣል ላይ ሲሆኑ ሩሲያም ተመሳሳይ እርምጃ በመውሰድ ላይ ናት።