ሩሲያ በሞስኮ የካናዳ አምባሳደርን ማብራሪያ እንዲሰጡ ጠራች
ካናዳ ሩሲያ ከዩክሬን ጋር ወደ ጦርነት መግባቷን ተከትሎ በ60 ሩሲያዊያን ላይ ማዕቀብ ጥላለች
አምባሳደሩ የተጠሩት በካናዳ የሩሲያ ኢምባሲ ላይ ተቀጣጣይ ነገር መወርወሩን ተከትሎ ነው
ሩሲያ ከዩክሬን ጋር ወደ ጦርነት መግባቷን ተከትሎ ከተለያዩ ሀገራት ከተቃውሞ በላይ የሆኑ ክስተቶችን ያስተናገደች ሲሆን ካናዳን ጨምሮ በርካታ የምዕራባውያን ሀገራት ማዕቀቦች ተጥለውባታል።
ከዚህ ባለፈ በትናንትናው ዕለት በካናዳ ኦታዋ ባለው የሩሲያ ኢምባሲ ላይ በተለምዶ ሞሎቶቭ ኮክቴይል የሚባል ስያሜ ያለው ተቀጣጣይ ነገር ተጥሏል።
ይህን ተቀጣጣይ ነገር የጣለው ሰው እስካሁን ያልታወቀ ሲሆን በአደጋው የተጎዳ ሰው ስለመኖሩ እና አለመኖሩ እስካሁን አልተገለጸም።
ድርጊቱ ሩስያን አስቆጥቷል የተባለ ሲሆን የካናዳ መንግስት ድርጊቱን የፈጸመውን ግለሰብ ሊያውቅ እና አደጋውን ሊያስቆም እንደሚገባ ሞስኮ አስታውቃለች።
የሩሲያ ውጭ ጉዳይ ሚንስቴርም በሞስኮ ያሉት የካናዳ አምባሳደር ስለጉዳዩ እንዲያብራሩለት እንደጠራ ታስ የተሰኘው ሚዲያ ዘግቧል።
ካናዳ ሩሲያ ከዩክሬን ጋር ወደ ጦርነት መግባቷን ተከትሎ በ60 ሩሲያዊያን ላይ ማዕቀብ ጥላለች።
ሩሲያ በበኩሏ በካናዳ ለተጣለባት ማዕቀብ ምላሽ በ55 ካናዳዊያን ላይ ወደ ሞስኮ እንዳይገቡ እና በሩሲያ ያላቸው ሀብት እንዳይንቀሳቀስ ተመሳሳይ ማዕቀብ መጣሏ ይታወሳል።
የሩሲያ ዩክሬን ጦርነት ከተጀመረ ሰባት ወራት ሊሞላው ጥቂት ቀናት የሚቀሩት ሲሆን በጦርነቱ ከ10 ሚሊዮን በላይ ዩክሬናዊያን ወደ ጎረቤት ሀገራት ሲሰደዱ ለዘመናት የተገነቡ መሰረተ ልማቶችም እየወደሙ ይገኛሉ።