የሩሲያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በሀገሪቱ ያሉትን የፖላንድ አምባሳደር ጠራ
በፖላንድ የሩሲያ አምባሳደር ከዩክሬን ስደተኞች ቀይ ቀለም ያለው ቁስ ተወርውሮባቸው ነበር
ዲፕሎማቱ ከተወረወረባቸው በኋላ በሩሲያ ያሉት የፖላንድ አምባሳደር ለማብራሪያ ተጠርተዋል
ከሰሞኑ በፖላንድ የሚገኙት የሩሲያ አምባሳደር ከስደተኛ ዩክሬናውያን ተቃዋሚዎች በተወረወረ ቀይ ቀለም መጥለቅለቃቸውን ተከትሎ ሩሲያ የፖላንድን አምባሳደር ለማብራሪያ ጠራች፡፡
አምባሳደር ሰርጊ አንድሬቭ በ2ኛው የዓለም ጦርነት ለተሰው የሃገራቸው ወታደሮች የአበባ ጉንጉን በመስቀመጥ ላይ ሳሉ ነበር ጥቃት የደረሰባቸው፡፡ ይህንን ተከትሎም በሩሲያ የሚገኙት የፖላንድ አምባሳደር ማብራሪያ እንዲሰጡ ተጠርተዋል፡፡
ከፖላንዱ አምባሳደር በተጨማሪም በሩሲያ የአሜሪካ አምባሳደር ጥሪ እንደተደረገላቸው ተገልጿል፡፡ በፖላንድ የሚገኘው የሩሲያ ኤምባሲ እንዳስታወቀው ፖላንድ ኤምባሲ እንደምትዘጋ ካልገለጸች በስተቀር ሞስኮ ኤምባሲ የመዝጋት ሃሳብ የላትም፡፡
አምባሳደር ሰርጊ ሩሲያ ሰኞ ዕለት ያከበረችውን የድል ቀን ታሳቢ በማድረግ በ2ኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ለተሰው የሃገራቸው ወታደሮች መታሰቢያ የሚሆን የአበባ ጉንጉን በማስቀመጥ ሳሉ ነው በተቃዋሚ ዩክሬናውያን በተወረወረ ቀይ ቀለም መጥለቅለቀቸው ይታወሳል፡፡
ዋርሶ በሚገኘው የሩሲያ ወታደሮች የመቃብር ስፍራ የተገኙት ዩክሬናውያን ስደተኞች እና ደጋፊዎቻቸው አምባሳደር ሰርጊንና ሌሎች አጅበዋቸው የነበሩ የሩሲያ ዲፕሎማቶችን አጥቅተዋል፡፡
ጥቃቱ "ኒዮ- ናዚ" ባሏቸው አካላት መፈጸሙንም ነው የሩሲያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ማሪያ ዛካሮቫ በቴሌግራም ገጻቸው ያስታወቁት፡፡ የዩክሬንን ባንዲራ ይዘው የወጡት ተቃዋሚዎቹ "ፋሽስት ፋሽስት" እያሉ ሩሲያን ያወግዙ ነበር፡፡
አምባሳደር ሰርጊ በጥቃቱ የከፋ ጉዳት እንዳላስተናገዱ ለሃገራቸው ሚዲያዎች ተናግረዋል፡፡
ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በዩክሬን መስዋዕትነት በመክፈል ላይ ያሉ የሀገራቸውን ወታደሮች
ያወደሱ ሲሆን ምዕራባውያን ዩክሬንን ተጠቅመው ሩሲያን የመውረር እቅድ እንደነበራቸው አስታውቀዋል፡፡በጦርነቱ 12 ሚሊዮን ገደማ ዩክሬናውያን የመኖሪያ ቀያቸውን ለቀው ለስደት መዳረጋቸው ይነገራል፡፡