አምባሳደር ሰርጊ በ2ኛው የዓለም ጦርነት ለተሰው የሃገራቸው ወታደሮች የአበባ ጉንጉን በመስቀመጥ ላይ ነበሩ
በፖላንድ የሩሲያ አምባሳደር ሰርጊ አንድሪቭ ከስደተኛ ዩክሬናውያን ተቃዋሚዎች በተወረወረ ቀይ ቀለም ተጥለቀለቁ፡፡
አምባሳደር ሰርጊ ሩሲያ ዛሬ ያከበረችውን የድል ቀን ታሳቢ በማድረግ በ2ኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ለተሰው የሃገራቸው ወታደሮች መታሰቢያ የሚሆን የአበባ ጉንጉን በማስቀመጥ ሳሉ ነው በተቃዋሚ ዩክሬናውያን በተወረወረ ቀይ ቀለም ለመጥለቅለቅ የበቁት፡፡
ዋርሶ በሚገኘው የሩሲያ ወታደሮች የመቃብር ስፍራ የተገኙት ዩክሬናውያን ስደተኞች እና ደጋፊዎቻቸው አምባሳደር ሰርጊንና ሌሎች አጅበዋቸው የነበሩ የሩሲያ ዲፕሎማቶችን አጥቅተዋል፡፡
ምዕራባውያን ዩክሬንን ተጠቅመው ሩሲያን ለመውረር አቅደው ነበር - ፑቲን
ጥቃቱ "ኒዮ- ናዚ" ባሏቸው አካላት መፈጸሙንም ነው የሩሲያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ማሪያ ዛካሮቫ በቴሌግራም ገጻቸው ያስታወቁት፡፡
የዩክሬንን ባንዲራ ይዘው የወጡት ተቃዋሚዎቹ "ፋሽስት ፋሽስት" እያሉ ሩሲያን ያወግዙ ነበር፡፡
አምባሳደር ሰርጊ በጥቃቱ የከፋ ጉዳት እንዳላስተናገዱ ለሃገራቸው ሚዲያዎች ተናግረዋል፡፡
ሩሲያ ዛሬ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ናዚ ጀርመንን ያሸነፈችበትን ቀን በተለያዩ ወታደራዊ ትዕይንነቶች አክብራለች፡፡
በስነ ስርዓቱ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በዩክሬን መስዋዕትነት በመክፈል ላይ ያሉ የሃገራቸውን ወታደሮች ያወደሱ ሲሆን ምዕራባውያን ዩክሬንን ተጠቅመው ሩሲያን የመውረር እቅድ እንደነበራቸው አስታውቀዋል፡፡
ሩሲያ በዩክሬን ልዩ ዘመቻ ማካሄድ ከጀመረች 75 ቀናት ተቆጥረዋል፡፡ ዘመቻውን ተከትሎ ከ6 ሺህ በላይ ማዕቀቦች በምዕራባውያን ሃገራትና አጋሮቻቸው የተጣሉባትም የአጸፋ እርምጃ በመውሰድ ላይ ትገኛለች፡፡
በጦርነቱ 12 ሚሊዮን ገደማ ዩክሬናውያን የመኖሪያ ቀያቸውን ለቀው ለስደት መዳረጋቸው ይነገራል፡፡