ሩሲያ ከምዕራቡ ዓለም ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንደምታቋርጥ ዛተች
የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር "የናንሲ ፔሎሲ የታይዋን ጉብኝት ግጭት ቀስቃሽና ውጥረት የሚጨምር ነው" ብሏል
ሩሲያ “እጅግ ከከረረ ሁኔታ ላይ ደርሰናል“ እናም ከአሜሪካ ጋር ወደ ግጭት ልናመራ እንችላለን ማለቷ አይዘነጋም
ሩሲያ ከምዕራቡ ዓለም ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንደምታቋርጥ ዛተች፡፡
የምዕራቡ ዓለም፡ ሞስኮን "የሽብርተኝነት ደጋፊ" በማለት ለመፈረጅ በዝግጅት ላይ መሆኑ የገባት ሩሲያ፤ ከምዕራቡ ዓለም ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንደምታቋርጥ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሯ በኩል ግልጽ አድረጋለች፡፡
የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ፤ አሜሪካ በዩክሬን ጉዳይ ቀጥተኛ ተሳትፎ አድርጋለች ሲልም ከሰዋል።
"የአሜሪካ ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ ወደ ታይዋን ሊያደርጉት ከሚችሉት ጉብኝት ጋር የተያያዙ ሁሉም ነገሮች እጅግ ግጭት ቀስቃሽ እና ውጥረቶች የሚጨምሩ ናቸው "ም ብሏል የሚኒስቴሩ መግለጫው፡፡
አሜሪካ እየተባባሰና እየሻከረ ከመጣው የአሜሪካ-ሩሲያ ዝምድና ጋር በተገናኘ ባሳለፍነው አርብ በአሜሪካ ግምጃ ቤት አማካኝነት አዲስ ማዕቀብ መጣሏ የሚታወስ ነው፡፡
ግምጃ ቤቱ “በምርጫ ጣልቃ ገብነት እና በሳይበር እንቅስቃሴዎች በሁለት ሩሲያውያን እና በአራት አካላት ላይ ማዕቀብ መጣሉን” አስታውቋል።
የአሜሪካ ግምጃ ቤት፤ ቀደም ሲል በዋሽንግተን ማዕቀብ ተጥሎበት በነበረው በሩሲያው ፖለቲከኛ ሱሌይማን ካሪሞቭ የሚተዳደረውና በአሜሪካ መቀመጫው ባደረገው ኩባንያ ላይ ባሳለፍነው ወር ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ ንብረትን ማገዱንም ገልጿል።
ሩሲያ “እጅግ ከከረረ ሁኔታ ላይ ደርሰናል“ እናም ከአሜሪካ ጋር ወደ ግጭት ልናመራ እንችላለን ስትል በቅርቡ ማስጠንቀቋ አይዘነጋም፡፡
በሁለቱ ኃያላን ሃገራት መካከል ያለው ግንኙነት ምንም እንኳን ዲፕሎማሲያዊና ሌሎች ግንኙነቶቻቸውን ሙሉ በሙሉ ባያቋርጡትም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ እየሻከረ መጥቷል፡፡
በተለይ ሩሲያ በዩክሬን ̒“ልዩ” ያለችውን ዘመቻ ከጀመረች በኋላ ግንኙነታቸው ከመሻከር አልፎ ወደ ውጥረት ተሸጋግሯል፡፡
ሆኖም ከዩክሬን ቀውስ በኋላም ቢሆን በራቸውን ለኮሚዩኒኬሽን ዝግ ሳያደረጉ ሲነጋገሩ መቆየታቸው ይታወቃል፡፡
ይሁን እንጂ አሁን ላይ፤ የሩሲያ-አሜሪካ ግንኙነት ወደሚያሰጋ ደረጃ መሸጋገሩን የሩሲያው የዜና ወኪል አር.አይ.ኤ በቅረቡ የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭን ጠቅሶ መዘገቡ የሚታወስ ነው፡፡
ቃል አቀባዩ "ሞስኮ እና ዋሽንግተን ወደ ግጭት ሊያመሩ ከሚችሉበት ምእራፍ ላይ ደርሰዋል" ብለዋል፡፡
ፔስኮቭ “አሜሪካ የሩሲያን የደህንነት ስጋቶች ለመፍታት ፈቃደኛ አለመሆኗ በዶንባስ ልዩ ዘመቻ ለማድረግ ምክንያት ሆኗል" ሲሉም ነበር የተናገሩት፡፡
"ከአሜሪካ ጋር ያለውን ግንኙነት መደበኛ ለማድረግ ብቸኛው መንገድ የዋሽንግተን የበላይነትን መተው እና ሞስኮ በማንም ላይ ጥገኛ እንደማትሆን መገንዘብ ብቻ ነው" ሲሉም አክለዋል፡፡
አሜሪካ ቀደም ባለው የቀዝቃዛው ጦርነት ወቅትም ቢሆን በሩሲያም ሆነ በማንኛውም ሀገር እንዲህ አይነት ከባድ እርምጃዎች አልወሰደችም ያሉት ቃል አቀባዩ ፔስኮቭ፤ አሜሪካ እና አጋሮቿ አሁን በሩሲያ ላይ የሚያዘንቧቸው ማዕቀቦች የሚጎዱት ሩሲያን ብቻ ሳይሆን መዕቀብ የሚጥሉትንም ጭምር መሆኑ ሊታወቅ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡