የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት እንዴት ሊጠናቀቅ ይችላል?
በጦርነቱ ሩሲያ የምትሸነፍ ከሆነ በተመድ ያላትን ድምጽን በድምጽ የመሻር መብት ታጣለች የሚሉም አሉ
ጦርነቱ በሩሲያ አሸናፊነት ከተጠናቀቀ ምእራባውያን በዓለም ላይ ያላቸው የበላይነት ሊጠናቀቅ እንደሚችል ምሁራኑ ይናራሉ
ዩክሬን የሰሜን አትላንቲክ ቃል ኪዳን ጦር ወይም ኔቶን እቀላቀላለሁ ማለቷን ተከትሎ ሩሲያ የጀመረችው “ልዩ ወታደራዊ ዘመቻ” ስድስት ወራት ሊሆነው ቀናት ይቀሩታል፡፡
መሬት ላይ ሁለቱ ሀገራት ጦርነት ቢጀምሩም ከዚህ ጦርነት ጀርባ ግን የተለያዩ ግልጽ እና ስውር አሰላለፎች ይዘዋል፡፡
ጦርነቱ ከተጀመረ ጊዜ አንስቶ የተከሰቱ የዓለም ኢኮኖሚ፣ ዲፕሎማሲ፣ ፖለቲካ እና ሌሎች ለውጦችን በማየት ጦርነቱ በዩክሬን መሬት ላይ ይካሄድ እንጂ የዓለም ጦርነት ነው የሚሉ አስተያየቶች ይደመጣሉ፡፡
- ሩሲያ ከ100 በላይ አሜሪካ ሰራሽ "HIMARS" ሮኬቶችን “አወደምኩ” አለች
- ሩሲያ “ብቻዋን አትቀርም፤አታፈገፍግምም” ሲሉ ፕሬዝደንት ፑቲን ምእራባውያንን አስጠነቀቁ
ይህ የባለብዙ ወገን ጦርነት ለተጨማሪ ጊዜ የሚቀጥል ከሆነ አይገመቴ ክስተቶች ሊከሰቱ እንደሚችሉ ግምቶች እየወጡ ሲሆን ተፋላሚዎች ጦርነቱን በድል ለማጠናቀቅ ይጠቅመናል ያሏቸውን የዲፕሎማሲ እና የጦር መሳሪያ ሸመታው እንደቀጠለ ነው፡፡
ይህ ጦርነት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ዓለምን እየጎዳ በመሆኑ ጦርነቱ የማይመለከተው ሀገር እና ተቋም የለም በሚል ሁሉም ከጦርነቱ ለማትረፍ የሚችለውን በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡
ጦርነት እንዴት ሊጠናቀቅ ይችላል? የጦርነቱ ውጤቶችስ ምን ምን ሊሆኑ ይችላሉ? አል ዐይን አማርኛ በዚህ ጉዳይ ላይ የዓለም አቀፍ ግንኙነት ምሁራንን ጠይቋል፡፡
ረዳት ፕሮፌሰር እምቢአለ በየነ በባህር ዳር ዩንቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር የሩሲያ ዩክሬን ጦርነት በሩሲያ አሸናፊነት መጠናቀቁ አይቀርም ይላሉ፡፡
በአሜሪካ አስተባባሪነት አውሮፓ ህብረት እና ሌሎች አጋራ ሀገራት በሩሲያ ላይ በጣም ብዙ ማዕቀቦችን ቢጥሉም ማዕቀቦቹ ከሩሲያ ይልቅ ማዕቀብ የጣሉ ሀገራትን በበለጠ እየጎዳ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ እንኳን የአሜሪካ እና አውሮፓ ሀገራት ኢኮኖሚ እየተጎዳ ነው ያሉት ረዳት ፕሮፌሰር እምቢአለ ጦርነቱ ተጨማሪ ወራትን በቀጠለ ቁጥር የበለጠ እየተጎዱ የሚሄዱት ራሳቸው ምዕራባዊያን ይሆናሉ ብለዋል፡፡
ምሁሩ እንደሚሉት ሩሲያ ጦርነቱን የጀመረችው ኔቶ ወደ ሞስኮ የበለጠ እየቀረበ መምጣቱን በመቃወም በመሆኑ እና የህልውና ጦርነት በመሆኑ የጦርነቱ አሸናፊ መሆኗ የማይቀር ነው፡፡
ኔቶ በተዘዋዋሪ ሩሲያን እየተዋጋ መሆኑን የሚናገሩት መምህሩ ምዕራባዊያን ሩሲያን ማንበርከክ ከቻሉ ቀጣይ ኢላማቸው ቻይና ትሆናለች፣ ይህ ጦርነት በሩሲያ አሸናፊነት እንዲጠናቀቅም ቻይና እና የምዕራባዊያን የበላይነትን የማይደግፉ ሌሎች ሀገራት በቀጥታ እና በተዘዋዋሪ ድጋፍ በማድረግ ላይ ናቸውም ብለዋል፡፡
እየጨመረ በመጣው የነዳጅ ዋጋ ምክንያት በተለያዩ የአውሮፓ ሀገራት የስራ አድማ እና መሰል እንቅስቃሴዎች እየጨመሩ ነው የሚሉት መምህሩ ነዳጅ የበለጠ እየተወደደ እና ቀዝቃዛ ወራቶች ሲመጡ አውሮፓ በራሷ ጉዳይ ቢዚ ትሆናለችም ብለዋል።
አውሮፓውያን በኑሮ ውድነቱ እየተፈተኑ ሲመጡ በውስጥ ጉዳያቸው ቢዚ መሆናቸው አይቀርም የሚሉት ረዳት ፕሮፌሰር እምቢአለ በዩክሬን ጉዳይ እየተከፋፈሉ ይሄዳሉ፣ ይህ ሲሆን ሩሲያ የበለጠ ድል አስመዝግባ ጦርነቱን በምትፈልገው መንገድ ልትቋጨው ትችላለችም ሲሉ ግምታቸውን አክለዋል።
ሌላኛው በዓለም አቀፍ ግንኙነት እና ፖለቲካል ሳይንስ መምህር እያሱ ሀይለሚካኤል ጦርነቱ የዓለምን ኢኮኖሚ እና የፖለቲካ የበላይነትን ለመቆጣጠር የሚደረግ ጦርነት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የዩክሬን ጉዳይ ለጦርነቱ መጀመር መነሻ ሆነ እንጂ ምዕራባዊያን በበላይነት የተቆጣጠሩትን ዓለም ለማስቀጠል ዋነኛ ተቀናቃኝ ናት ያሏትን ሩሲያን በመክበብ ነጥሎ የመምታት እቅዳቸው ቀደም ብሎ የተነደፈ እንደነበርም መምህር እያሱ አክለዋል፡፡
የምዕራባዊያንን የበላይነት ለማስቀጠል የተመሰረተው ኔቶ ወደ ሩሲያ ለመቅረብ የቻለውን ሁሉ ሲያደርግ ቆይቷል የሚሉት መምህር እያሱ ዩክሬንን ከሩሲያ የመነጠል ስራው የተጀመረው ከስምንት ዓመት በፊት የሩሲያ ደጋፊ እንደሆኑ የሚነገርላቸው የቀድሞው የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቪክተር ያኒኮቪችን ህዝባዊ አመጽ እንዲነሳባቸው በማድረግ ከስልጣን እንዲለቁ ከተደረገ ጀምሮ እንደነበርም ተናግረዋል፡፡
ዩክሬን ከሩሲያ እጅ የወጣችው በዚህ ጊዜ ነበር፣ ከዛ ጊዜ አንስቶም ኔቶ ከዚህ በፊት የተደረጉ ስምምነቶችን በመጣስ ወደ ሞስኮ የበለጠ የመቅረብ እንቅስቃሴውን በመግፋቱ እና ሩሲያ የበለጠ የደህንነት ስጋት እየተሰማት ሲመጣ ከዩክሬን ግዛቶች ወደ ራሷ የመጠቅለል ስራዎችን ስትሰራ መቆየቷን ተናግረዋል፡፡
ይህ ጦርነት ከተጀመረ ቆይቷል የሚሉት መምህር እያሱ በዩክሬን ምድር እየተካሄደ ያለው የባለብዙ መልኩ ይህ ጦርነት አሸናፊ በቀጣይ በዓለም ላይ ብዙ ነገሮች ላይ ለውጥ እንደሚያመጣ ተናግረዋል፡፡
ጦርነቱ ከተጀመረ ጊዜ አንስቶ በዓለም ላይ የምግብ እና ነዳጅ ዋጋን እንዲጨምር ማድረጉ በብዙ ሀገራት ላይ ብዙ አይነት ለውጦችን ሊያስከትል እንደሚችል የሚናገሩት መምህር እያሱ ጦርነቱን ተከትሎ በሀገራት ላይ የሚያደርሰው የኑሮ ውድነት ህዝባዊ አመጽን በመቀስቀስ የመንግስታት ለውጥ እንዲመጡ ሊያደርግም ይችላል ብለዋል፡፡
በአጠቃላይ ይህ ጦርነት በዓለማችን ላይ አዲስ የሀይል አሰላለፍ ሊፈጠር የሚችልበት እና ዓለም ከምዕራባዊያን የበላይነት ልትላቀቅ የምትችልበት መንገድ ሊፈጠር እንደሚችልም ተናግረዋል፡፡
በሌላ መልኩ ደግሞ በቀዝቃዛው ጦርነት ወቅት እንደተደረገው የዓለም የበላይነትን ለመቆጣጠር በየአህጉራቱ አጋር መንግስታትን ለመፍጠር የእጅ አዙር ጦርነቶች፣ የመንግስት ግልበጣ ሙከራዎች እና ሌሎች የሀይል አሰላለፎች ሊከሰቱ እንደሚችሉም መምህር እያሱ ግምታቸውን አስቀምጠዋል፡፡
ጦርነቱ አንድም በነሩሲያ ቻይና ቡድን አሸናፊነት ሁለተኛው በአሜሪካ አውሮፓ ህብረት ቡድን አሸናፊነት አልያም ጦርነቱ በተኩስ አቁም ስምምነት ሊቋጭ እንደሚችልም መምህር እያሱ ጠቁመዋል።
ይህ በዚህ እንዳለ ግን ሩሲያ በጦርነቱ ከተሸነፈች የእነ ጀርመን ህብረት በሁለተኛው የዓለም ጦርነት የደረሰበትን ሽንፈት ተከትሎ እንዲከፍል የተወሰነበት የካሳ ክፍያ አይነት ውሳኔዎች ሊወሰኑ እንሰሚችልም አክለዋል።
ከዚህ በተጨማሪም ሩሲያ ሽንፈትን ካስተናገደች በጸጥታው ምክር ቤት ያላት ድምጽን በድምጽ የመሻር መብት ልታጣ እንደምትችልም ተናግረዋል ።
በበዩክሬን መሬት ላይ እየተካሄደ ያለው ጦርነት አሸናፊ ቡድን ከፍተኛ ሸማች ህዝብ ያላት፣ የተፈጥሮ ማዕድናት እና ሌሎች እድሎች ባለቤት የሆነችው አፍሪካን ለመቆጣጠር እና በሚፈልገው መንገድ ሀብቷን ለመጠቀም ሲል በየቦታው አዳዲስ ግጭቶችን ሊፈጥር፣ መፍትሄ ያላገኙ ነባር አለመግባባቶችን እንደ አዲስ ሊቀሰቅስ እና ተጨማሪ ችግሮችን ሊፈጥር ይችላልም ብለዋል፡፡