የዩክሬን ጥቃት ኪየቭ መልሶ ማጥቃት መጀመሯን ግልጽ አላደረገም
የሩሲያ ጦር በዶኔትስክ ግንባር የዩክሬንን ጥቃት ማክሸፉን እና በመቶዎች የሚቆጠሩ ወታደሮችን መግደሉን ተናግሯል።
ዩክሬን በበኩሏ ሞስኮን የውሸት ወሬ አሰራጭታለች ስትል ከሳለች።
የሩስያ የመከላከያ ሚንስቴር እንዳስታወቀው ዩክሬን እሁድ ጠዋት በደቡባዊ ዶኔትስክ ስድስት ሜካናይዝድ እና ሁለት ታንክ ሻለቃዎችን በመያዝ ጥቃት አድርጋለች።
ሞስኮ ዩክሬን በሩሲያ ቁጥጥር ስር በምትገኘው ግዛት ውስጥ ሾልካ ለመግባት እንደምትፈልግ ስትጠራጠር መቆየቷን ገልጻለች።
"ጠዋት ላይ ጠላት በደቡብ ዶኔትስክ አቅጣጫ በግንባሩ አምስት ዘርፎች ላይ መጠነ ሰፊ ጥቃትን ከፍቷል" ሲል የመከላከያ ሚንስቴር በቴሌግራም ባወጣው መግለጫ ተናግሯል።
"የጠላት ዓላማ መከላከያችንን ሰብሮ መግባት ነበር። በእሱ እሳቤ በግንባሩ ደካማ በሆነ አካባቢ ላይ ነው" በማለት ገልጿል።
"ጠላት ተግባሩን አላሳካም። ምንም ስኬት አልነበረውም" በማለት ጥቃቱ መክሸፉን ተናግሯል።
ሮይተርስ የሩስያን መግለጫ ወዲያውኑ ማረጋገጥ አለመቻሉን ጠቅሷል።
የዩክሬን የምድር ጦር አዛዥ ኦሌክሳንደር ሲርስኪ የዩክሬን ኃይሎች በሰሜናዊ ዶኔትስክ ውስጥ ለረጅም ጊዜ ፉክክር በነበረባት ባክሙት ከተማ አቅራቢያ "ወደ ፊት መጓዛቸውን" ቀጥለዋል ብለዋል።
ሆኖም በመልሶ ማጥቃቱ ላይ ምንም አይነት አስተያየት አልሰጡም።
የዩክሬን የስትራቴጂክ ኮሙኒኬሽን ማዕከል የሩስያን መግለጫ በቀጥታ ባይጠቅስም፤ ሩሲያ ውሸት ማሰራጨት እንደምትፈልግ ተናግሯል።
በ15 ወራት ጦርነት የተያዘባትን ግዛት ለማስመለስ ለወራት ቃል ስትገባ የቆየው የዩክሬን ጥቃቱ የመልሶ ማጥቃት መጀመርን ይወክላል ወይስ አይወክል የሚለው ወዲያውኑ ግልጽ አልሆነም።