አሜሪካ ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ከሩሲያ ጋር መደራደር እንደምትፈልግ ገለጸች
አሜሪካ በኑክሌር ጦር መሳሪያ ጉዳይ ከሩሲያ ጋር መደራደር እንደምትፈልግ አስታውቃለች
ሩሲያ የኑክሌር ጦር መሳሪያን ለጎረቤት ሀገራት ለማስታጠቅ መወሰኗ ዋሸንግተንን እንዳሳሰበ ተገልጿል
አሜሪካ ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ከሩሲያ ጋር መደራደር እንደምትፈልግ ገለጸች።
ሩሲያ ከሁለት ወር በፊት ከዋሸንግተን ጋር የተፈራረመችውን የኑክሌር ጦር መሳሪያ እቀባ ስምምነት ማፍረሷን ማስታወቋ ይታወሳል።
በዚህ ስምምነት መሰረት አሜሪካ እና ሩሲያ የኑክሌር ጦር መሳሪያ ፉክክር እንደማያደርጉ፣ ለሌሎች ሀገራት እንደማያስታጥቁ፣ የኑክሌር ጦር መሳሪያ መረጃዎችን ሙለዋወጥ እና የኑክሌር ጉዳቶችን የመቀነስ ግዴታ ነበረባቸው።
አሜሪካ ለዩክሬን የጦር መሳሪያ ማስታጠቋ እና አይነተ ብዙ ማዕቀቦች መጣሏን ተከትሎ ሩሲያ ከዚህ ስምምነት ራሷን ማግለሏን ፕሬዝዳንት ፑቲን ከሁለት ወር በፊት ይፋ አድርገዋል።
የፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የደህንነት አማካሪ ጃክ ሱልቪያን እንዳሉት ዋሽንግተን ከሞስኮ ጋር ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ሙደራደር ትፈልጋለች ሲሉ መናገራቸውን ዩሮ ኒውስ ዘግቧል።
አሜሪካ ከሩሲያ ጋር በኑክሌር ጦር መሳሪያ ጉዳይ ያለቅድመ ሁኔታ ለመደራደር ዝግጁ መሆኗንም አማካሪው ጠቅሰዋል።
ሩሲያ ከዚህ በፊት ከነበረው ስምምነት ብትወጣም ዋሸንግተን ከሞስኮ ጋር አዲስ ስምምነት ለመፈራረም ዝግጁ እንደኮነችም ተገልጿል።
ከፈረንጆቹ 2019 ጀምሮ ሁለቱ ሀገራት ስለ ኑክሌር ጦር መሳሪያ አዳዲስ ክስተቶች ምንም አይነት መረጃ የማይለዋወጡ ሲሆን ይህም ዋሸንግተንን አሳስቧል ተብሏል።
በሌላ በኩል የቻይና የጦር መሳሪያ ቴክኖሎጂ በፍጥነት እያደገ መሆኑ እና ቤጂንግ ለውይይት ፈቃደኛ አለመሆኗም ሌላኛው ስጋት እንደሆነ ተገልጿል።
ቻይና በይፋ ያመነችው የኑክሌር ጦር መሳሪያ ብዛት 410 ነው ተብሎ ቢመዘገብም አሜሪካ ግን እስከ አንድ ሺህ ሊደርስ ፕችላል ስትል ጠቅሳለች።