ሩሲያ አራት የዩክሬን ክልሎችን በነገው እለት በይፋ ወደ ግዛቷ ልትቀላቅል ነው
አራት የዩክሬን አካባቢዎች በህዝበ ውሳኔ ሩሲያን መቀላቀልን መምረጣቸው ይታወሳል
ዶኔትስክ፣ ሉንሃስክ፣ ዛፖሪዚሃና ኬህርሶን ክልሎች በነገው እለት በይፋ የሩሲያ አካል ይሆናሉ
ሩሲያ በቁጥጥሯ ስር የሚገኙ አራት ዩክሬን ክልሎችን በነገው እለት በይፋ ወደ ግዛቷ ልትቀላቅል መሆኑን ክሬምሊን አስታወቀ።
በሩሲያ ቁጥጥር ስር የሚገኙ አራት የዩክሬን አካባቢዎች በህዝበ ውሳኔ ሩሲያን ለመቀላቀል መወሰናቸው ይታወሳል።
ህዝበ ወሳኔው መጠናቀቁን ተከትሎ የሞስኮ ደጋፊ ባለስልጣናት በሰጡት መግለጫ፤ ሉሃንስክ እና ዶኔትስክ ሪፐብሊኮች ጨምሮ ህዝበ ውሳኔ በተካሄደባቸው አራቱም አካባቢዎች የሚገኙ ዩክሬናውያን ሩሲያን ለመቀላቀል ድምጽ መስጠታቸውን አስታውቀዋል።
ይህንን ተከትሎም ሩሲያ በነገው እለት በክሬምሊን ቤተ መንግስት በሚካሄድ ስነ ስርዓት አራቱንም የዩክሬን አካባቢዎች በይፋ ወደ ግዛቷ እንምተቃቅል ተነግሯል።
የክሬምሊን ቃለ አቀባይ ዲሜትሪ ፔስኮቭ በሰጡት መግለጫ፤ በነገው እለት በታላቁ ክሬምሊን ቤተ መንግስት አዳዲሶቹን የሩሲያ አካባዎች በይሃ የማዋሃድ የፊርማ ስነ ስርዓት ይካሄዳል ብለዋል።
በፊርማ ስነ ስርዓቱም በዩክሬን ውስጥ የሚገኙት ዶኔትስክ፣ ሉንሃስክ፣ ዛፖሪዚሃ እና ኬህርሶን ክልሎች በይፋ የሩሲያ አካል እንደሚሆኑ ይጠበቃል።
በዩክሬን እንዲሁም በበርካታ የምዕራባውያን ሀገራት ውግዘት የደረሰበት ህዝብ ውሳኔ ከመስከረም 13 ስከ መስከረም 17 ድረስ በሩሲያ በተያዙ ግዛቶች መካሄዱ ይታወሳል።
ህዝበ ውሳኔው የተካሄደው በአራት የዩክሬን ግዛቶች ላይ ሲሆን፤ ሉሃንስክ እና ዶኔትስክ ሪፐብሊኮች ያካተተ ነበር።
የህዝበ ውሳኔው ድምጽ አሰጣጥ መጠናቀቁን ተከትሎ በተካሄደው ቆጠራም 96 በመቶ ዩክሬናውያን ሩሲያን ለመቀላቀል መወሰናቸውን የሞስኮ ደጋፊ ባለስልጣናት ገልጸዋል።
አራቱም የዩክሬን አካባቢዎች በህዝበ ውሳኔ ሩሲያን ለመቀላቀል መወሰናቸውን ተከትሎ ከፍተኛ ድንጋጤ ውስጥ የገባቸው ዩክሬን፤ የምዕራቡ ዓለም ትርጉም ያለው ወታደራዊ ድጋፍ ያድርግልኝ ስትል ተማጽናለች።
ሩሲያ በበኩሏ ሞስኮ፤ በሩሲያ ኃየሎች ስር የሚገኙትን የዶንባስ ግዛቶችን ለመከላከል ስትራቴጂካዊ የኒውክሌር ጦር ማሳሪያ ልትጠቀም እንደምትችል ማስጠንቀቋ ይታወሳል።
የቀድሞ የሩስያ ፕሬዝዳንት ዲሚትሪ ሜድቬዴቭ ህዝበ ውሳኔ በተካሄደባቸው የዶንባስ ግዛቶች ላይ የሚቃጣ ማንኛውንም አደጋ ለመከላከል ፤ አስፈላጊ ነው የሚባለው የትኛውም የጦር መሳሪያ በጥቅም ላይ ታውላለች ማለታቸው አይዘነጋም።