ዩክሬን በቤላሩስ መነጋጋር አልፈልግም ብላ ነበር
ሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ከጀመሩ በኋላ ዛሬ በይፋ ድርድር ለመጀመር መዘጋጀታቸውን አስታውቀዋል።
ከሩሲያ ጋር "በቤላሩስ የምናደርገው ድርድር የለም" ሲሉ የነበሩት የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ዛሬ ከሩሲያ ጋር በይፋ ሊነጋገሩ እንደሆነ አሳውቀዋል።
ዜለንስኪ ትናንትና ሞስኮ እና ኬቭ በቤላሩስ ሳይሆን በሌላ ቦታ መነጋገር እንዳለባቸው ሲገልጹ ቢቆዩም፤ በኋላ ላይ ግን ያለቅድመ ሁኔታ ለመነጋር መስማማታቸው ተነግሯል።
ይህንን ተከትሎም ዛሬ የሁለቱ ሀገራት ልዑካን በዩክሬንና ቤላሩስ ድንበር ተገናኝተው እንደሚደራደሩ ይፋ ሆኗል።
ዜለንስኪ፤ ቤላሩስ ሀገራቸው እንድትጠቃ ግዛቷንም ጭምር በመፍቀዷ ቤላሩስ ውስጥ ከሩሲያ ጋር የምንነጋገርበት ምክንያት የለም ብለው ነበር። ይሁንና ፕሬዝዳንቱ ውሳኔያቸው በመቀልበስ ንግግሩ እንዲጀመር መወሰናቸውን ጽ/ቤታቸው አስታውቋል፡፡
ፕሬዝዳንቱ በሰአታት ውስጥ የአቋም ለውጥ እንዴት አሰዩ ለሚለው በምክንያትነት የተቀመጠ ግልጽ ነገር ባይኖርም፤ የሩሲያ መጠነ ሰፊ ወታደራዊ ጥቃት የፈጠረው ተጽእኖ እንደሆነ እየተነገረ ነው።
ሩሲያ ቀደም ሲል የተለያየ ስብጥር ያለው ልዑክ ለድርድር ወደ ቤላሩስ መላኳ አስታውቃ እንደነበር አይዘነጋም። ወደ ቤላሩስ ያቀናው የሩሲያ ልዑክም ከውጭ ጉዳይ፣ ከመከላከያ ሚኒስቴር እና ከተለያዩ ተቋማት የተውጣጡ ተደራዳሪ አካላትን መያዙን የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሜትሪ ፔስኮቭ መናገራቸው ይታወሳል።
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ዜለንስኪ ለእንግሊዙ ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን የሚቀጥሉት 24 ሰዓታት እጅግ ወሳኝ ናቸው ማለታቸው ተሰምቷል።
የዩክሬን ጦር የትናንትናው ዕለት (ዕሁድ) እጅግ ከባድ እንደነበር ገልጾ የሩሲያ ጦር በሁሉም አቅጣጫዎች ድብደባ አድርጓል ብሏል። የዩክሬን ጤና ሚኒስቴር እስካሁን ህጻናትን ጨምሮ 352 ንጹሃን መገደላቸውን አስታውቋል።
በዩክሬንና ሩሲያ መካከል እየተካሄደ ያለውን ጦርነት ተከትሎ ይደረጋል የተባለው ድርድር እየተጠበቀ ነው።