ዩክሬን ከአሜሪካ በተለገሱ የጦር መሳሪያዎች ሩሲያን እንድትመታ ተፈቀደላት
የኔቶ አባል ሀገራት በለገሷቸው የጦር መሳሪያዎች ዩክሬን ከውጊያ ግንባሮች ያለፈ ጥቃት እንድትፈጽም እየፈቀዱ ነው
ሩሲያ በበኩሏ ከምዕራባዊያን ሀገራት በተለገሰ የጦር መሳሪያ ጥቃት ከተፈጸመብኝ መዘዙ ከባድ ነው ስትል አስጠንቅቃለች
ዩክሬን ከአሜሪካ በተለገሱ የጦር መሳሪያዎች ሩሲያን እንድትመታ ተፈቀደላት፡፡
ሶስት ዓመት የሆነው የዩክሬን-ሩሲያ ጦርነት በየጊዜው የተለያዩ ክስተቶችን እያስተናገደ እንደቀጠለ ይገኛል፡፡
ከምዕራባዊን ሀገራት በተለገሰ የጦር መሳሪያ ከሩሲያ ጋር እየተዋጋች ያለችው ዩክሬን ከውጊያ ግንባሮች ባለፈ በመሀል ሩሲያ ጥቃት ለማድረስ ፍላጎት ቢኖራትም ለጋሽ ሀገራት ሩሲያን በመፍራት ሳይፈቅዱ ቆይተዋል፡፡
የሩሲያ ጦር ተጨማሪ የዩክሬን ከተሞችን እየተቆጣጠረ መምጣቱን ተከትሎ ኪቭ ለጋሽ ሀገራት በመሀል ሩሲያ ጥቃት ለማድረስ የጦር መሳሪያዎቻቸውን እንድትጠቀም እንዲፈቅዱላት ስትጠይቅ ቆይታለች፡፡
ለዩክሬን ጥያቄም በርካታ ሀገራት ከብዙ ማቅማማት በኋላ ይሁንታቸውን እየሰጡ ሲሆን የተወሰኑ ሀገራት አሁንም አልፈቀዱም፡፡
ዴንማርክ፣ሆላንድ፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን እና ሌሎችም ሀገራት ዩክሬን ራሷን ለመከላከል በመሀል ሩሲያ ጥቃት እንድታደርስ የፈቀዱ ሀገራት ናቸው፡፡
ለዩክሬን ዋነኛ የጦር መሳሪያ ድጋፍ ሰጪ ሀገር የሆነችው አሜሪካ በተወሰነ ደረጃ የጦር መሳሪያዎቿን እንድትጠቀም ፈቅዳለች፡፡
ቪኦኤ እንደዘገበው ከሆነ ዩክሬን ከአሜሪካ በተለገሱ የጦር መሳሪያዎች በካርኪቭ አካባቢ ሩሲያን ማጥቃት እንደምትችል ፈቅዳለች፡፡
ኔቶ በበኩሉ ዩክሬን ከሩሲያ ጋር በምታደርገው ጦርነት የጦር መሳሪያዎቿን ያለ ገደብ መጠቀም እንድትችል ሊፈቀድ ይገባል ብሏል፡፡
ለዩክሬን የላኩት የጦር መሳሪያ የሩሲያን ግዛት እንዲመታ የፈቀዱ ሀገራት የትኞቹ ናቸው?
የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት በድርድር እንዲቋጭ ጥረቶች እየተደረጉ ቢሆንም ጦርነቱ አሁንም እንደቀጠለ ይገኛል፡፡
ከሁለት ሳምንት በኋላ በስዊዘርላንድ የሚደረግ ውይይት መድረክ የተዘጋጀ ሲሆን ሩሲያ በውይይቱ ላይ አለመጋበዟን ተከትሎ እንደ ቻይና እና ብራዚል ያሉ ተጽዕኖ ፈጣሪ ሀገራት መድረኩ ገለልተኛ ባለመሆኑ አስቀድመው እንደማይገኙ አሳውቀዋል፡፡
ዩክሬን በበኩሏ ከሩሲያ ጋር ለመደራደር በሀይል የወሰደቻቸውን ግዛቶች እንድትመልስ በቅድመ ሁኔታነት ያስቀመጠች ሲሆን ሩሲያ በበኩሏ ጦርነቱ የሚቆመው ዩክሬን በህዝበ ውሳኔ ወደ ሞስኮ ለተጠቃለሉ አራት ግዛቶች እውቅና ከሰጠች ብቻ ነው ብላለች፡፡