ዘለንስኪ ሩሲያ እና ቻይናን የሰላም ጉባኤን ዋጋ በማሳነስ ከሰሱ
ከሩሲያ ጋር ወግናለች በሚል ተደጋጋሚ ጥያቄ የሚነሳባት ቻይና ከሁለቱም ወገን እንዳልወገነች ትገልጻለች
የዩክሬኑ ፕሬዝደንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ ሩሲያ እና ቻይና በስዊዘርላንድ የሚካሄደውን የሰላም ጉባኤ ዋጋ ለማሳነስ እየሞከሩ ነው ሲሉ ከሰዋቸዋል
የዩክሬኑ ፕሬዝደንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ ሩሲያ እና ቻይና በስዊዘርላንድ የሚካሄደውን የሰላም ጉባኤ ዋጋ ለማሳነስ እየሞከሩ ነው ሲሉ ከሰዋቸዋል።
ቢቢሲ እንደዘገበው ሩሲያ ሌሎች ሀገራት በጉባኤው እንዳይሳተፉ እያከላከለች ነው፤ ቻይናም ይህንኑ እየሰራች ነው ብለዋል ዘለንስኪ።
በእስያ ሴኩሪቲ ስብሰባ ላይ የተገኙት ዘለንስኪ ከቻይና የመጡ "የሩሲያ መሳሪያ አካላት አሉ" ሲሉ ተናግረዋል።
ከሩሲያ ጋር ወግናለች በሚል ተደጋጋሚ ጥያቄ የሚነሳባት ቻይና ከሁለቱም ወገን እንዳልወገነች ትገልጻለች።
ቻይና የጦር መሳሪያ አካላትን ለሩሲያ ልካለች የሚል ክስ ነው እየቀረበባት ያለው። ከዚህ በተጨማሪም ቻይና ከፍተኛ መጠን ያለው ነዳጅ ከሩሲያ በመግዛት፣ በምዕራውያን ማዕቀብ ምክንያት ሊደርስባት የነበረው ጫና እንዲቀንስ ማድረጓ በምዕራባውያን ዘንድ አልተወደደም።
ዘለንስኪ የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስትር ልዮድ ኦስቲንን እና የቻይና መከላከያ ሚኒስትር ዶንግ ጁን በተገኘበት የሻንጋሪ ላ ዲያሎግ ላይ ሳይጠበቁ ተገኝተዋል። ዘለንስኪ ወደ እዚህ ስብሰባ የሄዱት የእስያ ሀገራት እንዲደግፏቸው ለማሳመን ነው ተብሏል።
የቀጣናው መሪዎችን ያገኙት ዘለንስኪ የልኡካን ቡድኖች በሰኔ መጨረሻ በሚካሄደው የሰላም ጉባኤ ላይ እንዲሳተፉ ጠይቀዋል።
ዘለንስኪ እንደገለጹት ከሆነ በሲዊዘርላንድ የሚካሄደው ይህ ስብሰባ በኑክሌር ሴኩሪቲ፣ በምግብ ዋስትና እና በሩሲያ የተያዙ የዩክሬን ህጻት መለለቀቅ ጉዳይ እንደሚያተኩር ተናግረዋል።
እስካሁን 106 ሀገራት ከፍተኛ የልኡካን ቡድን ወይም መሪዎችን እንልካለን ማለታቸውን ዘለንስኪ ተናግረዋል።
ሩሲያ በዚህ ስብሰባ ያልተጋበዘች ሲሆን ቻይና ደግሞ እንደማትገኝ ገልጻለች።
የሩሲያ ዩክሬን ሁለት አመት ያለፈው ሲሆን በምስራቅ ዩክሬን እየተደረገ ያለው ውጊያ አሁንም አንደቀጠለ ነው። ሩሲያ ባለፈው አመት በይፋ ወደግዛቷ የተጠቀለለቻቸውን አራት ግዛት ሙሉ በሙሉ እስከምትቆጣጠር ድረስ ጦርነቱን እንደምትገፋበት መግለጿ ይታወሳል።
አሁን ላይ 18 በመቶ የሚሆነው የዩክሬን ግዛት በሩሲያ ስር ሆኗል። ዩክሬን የተያዘባትን ቦታዎች ነጻ ለማውጣት ምዕራባውያን የጦር መሳሪያ እርዳታ እንዲያደርጉላት ጠይቃ፣ እርዳታው እየቀረበላት ይገኛል።
በቅርቡ የአሜሪካ ተወካዮች ምክርቤት የ61 ቢሊዮን ዶላር የጦር መሳሪያ ድጋፍ አጽድቋል።