የኮሚቴው ፕሬዝዳንት በመጪ የኦሎምፒክ ውድድሮች የዩክሬን ሰንደቅ ዓላማ መውለብለቡን እናረጋግጣለን ብለዋል
ዩክሬንን በቀጣይ የኦሎምፒክ ውድድሮች እንደሚያሳትፍ የዓለም ኦሎምፒክ ኮሚቴ አስታወቀ፡፡
የኮሚቴው ፕሬዝዳንት ቶማስ ባች በዩክሬን ጉብኝት አድርገዋል፡፡
በጉብኝቱ ከፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ ጋር የተወያዩ ሲሆን በመጪ የኦሎምፒክ ውድድሮች የዩክሬን ሰንደቅ ዓላማ መውለብለቡን እናረጋግጣለን ብለዋል፡፡
የሩሲያ ዩክሬን ጦርነት ከመጀመሩ በፊት ወደ ኪቭ አቅንተው የነበሩት ባች የዩክሬን አትሌቶች በፈረንሳይ እና ጣሊያን በሚካሄዱ ቀጣይ የኦሎምፒክ ውድድሮች እንደሚሳተፉ ነው የገለጹት፡፡ ለዚህም ድጋፍ ለማድረግ ቃል ገብተዋል፡፡
ኮሚቴው ሩሲያ እና ቤላሩስ በየትኞቹም አይነት ውድድሮቹ እንዳይሳተፉ ከአባልነት ጭምር አግዷል፡፡ እገዳው አሁን እንደሚቅጥል ለፕሬዝዳንት ዜሌንስኪ የተናገሩት ባች ከጦርነቱ በፊት ለዩክሬን ስናደርግ የነበረውን ድጋፍ በሶስት እጥፍ አሳድገን 7 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር እንሰጣለን ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ኮሚቴው ከአሁን ቀደም ለዩክሬን 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር ገደማ ድጋፍን ያደርግ ነበር፡፡
ስለ ጉብኝቱ እና ድጋፉ ያመሰገኑት ፕሬዝዳንት ዜሌንስኪ በበኩላቸው ሩሲያ በከፈተችው ጦርነት ምክንያት አብዛኞቹ የሃገሪቱ አትሌቶች መዝመታቸውን ገልጸው፤ 89 አትሌቶችና አሰልጣኞች መሞታቸውን 13 ገደማ ደግሞ በሩሲያ ጦር መማረካቸውን ተናግረዋል፡፡
በጦርነቱ ምክንያ የሩሲያ እና የቤላሩስ ስፖርታዊ ውድድሮች እውቅና መነፈጋቸውና አትሌቶቻቸውም ከውድድሮች ውጭ እንዲሆኑ መደረጉ የሚታወስ ነው፡፡
ከሩሲያ ጋር ውጊያ ላይ ያለችው ዩክሬን ኦሊምፒክን የማዘጋጀት ዕቅድ ነበራት፡፡ ሆኖም በጦርነቱ ምክንያት ማዘጋጀቱ ቀርቶ መሳተፉ በራሱ ችግር ሆኖባታል፡፡