እውን የዘንድሮው የአውሮፓ ሻምፒዮስ ሊግ የፍጻሜ ጨዋታ በሩሲያ ይካሄድ ይሆን?
ሩሲያ የሻምፒዮንስ ሊግ የፍጻሜ ጨዋታን ለመጨረሻ ጊዜ ያዘጋጀችው በፈረንጆቹ 2008 ነበር
የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር የፍጻሜ ጨዋታን በተመለከተ ለነገ አርብ አስቸኳይ ስብሰባ ጠርቷል
የዘንድሮውን የአውሮፓ ሻምፒዮስ ሊግ የፍጻሜ ጨዋታ የፊታችን ግንቦት 28 ቀን 2022 በሩሲያዋ ቅዱስ ፒተርስበርግ ከተማ ለማካሄድ መርሃ ግብር ወጥቶ ዝግጅቶች እየተደረጉ ነው፡፡
ይህም የዓለም ዋንጫን በ 2018 ላስተናገደችው ሩሲያ ትልቅ ዕድል ቢሆንም በአዘጋጇ ሃገር ሩሲያ እና ዩክሬን መካከል ጦርነት መቀስቀሱ የስፖርት ቤተሰቡ በጉጉት የሚጠብቀውን የፍጻሜ ጨዋታ መርሃ ግብር አጣብቂኝ ውስጥ ከቷል፡፡
ጨዋታው በተያዘለት መርሃ ግብር መሰረት ይካሄድ አይካሄድ ይሆን በሚል ብዙዎችን እያነጋገረ ነው፡፡
የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር (UEFA) የሥራ ኃላፊዎችም በሩሲያ እና ዩክሬን መካከል ያለው ፍጥጫ እየተባባሰ መምጣቱን ተከትሎ ከሰሞኑ ሲወያዩ ነበረ፡፡
ፍጥጫው ይበልጥ ተባብሶ ባለፉት 24 ሰዓታት ወደ ጦርነት መገባቱንም ተከትሎ የማህበሩ ፕሬዝዳንት አሌክሳንደር ሴፈሪን ለነገ አርብ አስቸኳይ ስብሰባ ጠርተዋል፡፡
አስቸኳይ ስብሰባው ጨዋታውን ለማካሄድ በሚያስችሉ ሁኔታዎች ዙሪያ ለመምከር ነው እንደ ማህበሩ መግለጫ፡፡ ጨዋታውን የተመለከተ ውሳኔ እንደሚያሳልፍ ይጠበቃል፡፡ ሆኖም በከተማዋ ይካሄድ አይካሄድ በሚለው ላይ እስካሁን የተሰጠ ውሳኔ የለም፡፡ ውሳኔውን ነገ እንደሚያሳውቅ ማህበሩ አስታውቋል፡፡
ማህበሩ ከአሁን ቀደም እንዲህ ዐይነት ሁኔታዎች አጋጥመውት ያውቃሉ፡፡ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት 2 የሻምፒዮንስ ሊግ የፍጻሜ ጨዋታዎችን አዘዋውሯል፡፡ በፈረንጆቹ 2020 በቱርክ ኢስታንቡል ሊካሄድ የነበረውን የፍጻሜ ጨዋታ ወደ ሊዝበን ፖርቹጋል ከዚያም ወደ ፖርቶ ማዘዋወሩ ይታወሳል፡፡
ቅዱስ ፒተርስበርግ ከአሁን ቀደም በጋዝፕሮም አሬና የ2018ቱን የዓለም ዋንጫ ጨምሮ የተለያዩ የፍጻሜ ጨዋታዎችን አስተናግዳለች፡፡
ግዙፉ የሩሲያ ነዳጅ አምራች ኩባንያ ጋዝፕሮምም ከአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር ጋር የስፖንሰርሺፕ ስምምነት አለው፡፡ ሆኖም ስምምነቱ በእንዲህ ዐይነት ሁኔታ የሚቀጥል አይመስልም፡፡
የእንግሊዙ ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን ሉዓላዊ ያሏትን ዩክሬንን በወረረችው ሩሲያ የአውሮፓን የፍጻሜ ጨዋታ ማካሄድ የሚታሰብ እንዳልሆነ ከሰሞኑ ተናግረዋል፡፡
የባለፈው ዓመት የውድድሩ የፍጻሜ ተፋላሚዎቹን ቼልሲ እና ማንችስተር ሲቲን ጨምሮ 4 የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ቡድኖች በሻምፒዮንስ ሊግ ጥሎ ማለፍ ጨዋታዎች በመሳተፍ ላይ ናቸው፡፡
ቼልሲ በፖርቹጋል ፖርቶ ድራጋዖ ስታዲዬም በተካሄደው የባለፈው ዓመት የፍጻሜ ጨዋታ ሲቲን በማሸነፍ ዋንጫውን ማንሳቱ ይታወሳል፡፡
ሩሲያ የሻምፒዮንስ ሊግ የፍጻሜ ጨዋታን ለመጨረሻ ጊዜ ያዘጋጀችው በፈረንጆቹ 2008 ነው፡፡ በወቅቱ ማንችስተር ዩናይትድ ቼልሲን በመለያ ምት ረትቶ ዋንጫውን ማንሳቱ አይዘነጋም፡፡
ጦርነቱን ተከትሎ በአውሮፓ የተለያዩ ሊጎች የሚሳተፉ አንዳንድ ቡድኖች የተለያዩ እርምጃዎችን መውሰዳቸውን እያስታወቁ ነው፡፡
በጀርመን ቡንደስሊጋ በመሳተፍ ላይ የሚገኘው ሻልክ 04 የዋና ስፖንሰሩን የጋዝፕሮምን ምልክት ከተጨዋቾቹ መለያ ላይ ለማንሳት መወሰኑን አስታውቋል፡፡