በሴኔጋል የዩክሬን ኤምባሲ ሴኔጋላዊያን ወደ ዩክሬን ሄደው መዋጋት ለሚፈልጉ የቅጥር ማስታወቂያ አወጣ
የሩሲያ ጦር ወደ ዩክሬን ከገባ ዛሬ ዘጠነኛ ቀኑን ይዟል
በዚህ ማስታወቂያ የተበሳጨችው ሴኔጋልም የዩክሬንን አምባሳደር ማብራሪያ እንዲሰጥ ጠርታለች
በሴኔጋል የዩክሬን ኤምባሲ ወደ ዩክሬን ሄደው መዋጋት ለሚፈልጉ ሴኔጋላዊያን የቅጥር ማስታወቂያ አወጣ።
ዩክሬን የሰሜን አትላንቲክ ቃልኪዳን ጦር ወይም ኔቶን እቀላቀላለሁ ማለቷን ተከትሎ ከሩሲያ ጋር ወደ መካረር ገብታ አሁን ላይ ወደ ይፋዊ ጦርነት ውስጥ ከገባች ዘጠኝ ቀናት ሆኗታል።
የሩሲያ ጦርም ዬክሬን ድንበርን አልፎ የተለያዩ ከተሞችን በመቆጣጠር ላይ ሲሆን ዛሬ ሌሊት ላይ በተደረገ ከባድ ውጊያ ዛፖሪዥያ የኒዩክሌር ጣቢያ በሩሲያ ኃይሎች ተይዟለ።
ጦርነቱን ብቻዋን እየተዋጋሁ ነው የምትለው ዩክሬን በየሀገራቱ ባሉ ኤምባሲዎቿ በኩል ለውጭ ሀገራት ዜጎች ለዩክሬን ተሰልፈው እንዲዋጉ የቅጥር ማስታወቂያዎችን በማውጣት ላይ ናት።
በዳካር የሚገኘው የዩክሬን ኢምባሲ በጎ ፈቃደኛ ሴኔጋላዊያን እና ሌሎች የውጭ ሀገራት ዜጎች ወደ ኬቭ አምርተው ከሩሲያ ጋር እየተደረገ ባለው ጦርነት እንዲዋጉ የቅጥር ማስታወቂያ አውጥቷል።
በዚህ የተበሳጨው የሴኔጋል ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በዳካር የዩክሬን አምባሳደር ዩሪ ፒቮቫሮቭ በጉዳዩ ዙሪያ ማብራሪያ እንዲሰጡ ጠርታለች።
የኢምባሲው ድርጊት የሀገራት የዲፕሎማሲ ግንኙነት ዙሪያ የወጣው የቬና ድንጋጌዎችን የሚጥስ ነው ስትል ሴኔጋል ከስሳለች።
ይሁንና ኤምባሲው ወደ ዩክሬን ሄደው እንዲዋጉ ያወጣወን የቅጥር ማስታወቂያ ቆይቶ ያጠፋ ቢሆንም በቀጣይ ምን አይነት እርምጃዎችን ሊወስድ እንደሚችል ግልጽ አይደለም በሚል የሴኔጋል ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገልጿል።
ሴኔጋል ተመድ የሩሲያን ዩክሬን ወረራ ለማስቆም በሚል በጠራው ጉባኤ ላይ የድምጸ ተዓቅቦ ማድረጓ ይታወሳል።