ቭላድሚር ፑቲን ወደ ስፍራው እንደማይጓዙ መገለጹ ይታወሳል
ሩሲያ፤ በ77 ኛው ተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ ለሚወክላት ልዑክ የቪዛ ጥያቄ ማቅረቧን አስታወቀች።
በአሜሪካ የሚገኘው የሩሲያ ኤምባሲ፤ በተመድ ጠቅላላ ጉባዔ ሩሲያን ለሚወክለው ቡድን የቨ ዛ ጥያቄ ማቅረቡን ገልጿል። ኤምባሲው ጥያቄውን ለአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ስለማቅረቡ የሩሲያው መገናኛ ብዙኃን ሩሲያ ቱዴይ ዘግቧል።
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ ሩሲያ የምትወከለው በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ ሰርጌ ላቭሮቭ መሆኑን አስቀድማ መግለጿ ይታወሳል።
77 ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ በፈረንጆቹ ከመስከረም 13 እስከ 20 እንደሚካሄድ የወጣው መርሃ ግብር ያመለክታል።
ሩሲያም በዚህ ስብሰባ ለሚሳተፉት ሰርጌ ላቭሮቭ እና ለልዑካቸው ወደ አሜሪካ የመግቢያ ቪዛ መጠየቁ ተሰምቷል።
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ዘንድሮ በሚካሄደው የተመድ ጠቅላላ ጉባዔ ላይ እንደማይገኙ ቀድመው መግለጻቸው ይታወሳል።
በዚህ መሰረት በጉባዔው ሩሲያን የሚወክሉት ከፑቲን ቀጥሎ ወዳጆቻቸው “ጠንካራው ዲፕሎማት” የሚሏቸው፤ ምዕራባውያን ደግሞ “አደገኛው” የሚሏቸው የዓለም አቀፍ ግንኙነት ምሩቁ ሰርጌ ላቭሮቭ ናቸው።
ሰርጌ ላቭሮቭ የሀገራቸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የሆኑት በአውሮፓውያኑ 2004 ነበር። የ 77 ዓመቱ ሰርጌ ላቭሮቭ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከመሆናቸው በፊት ለ 10 ዓመታት ማለትም ከአውሮፓውያኑ 1994 እስከ 2004 በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሩሲያ ቋሚ መልዕክተኛ ነበሩ።
ሩሲያን በተባበሩት መንግስታት ድርጅት 77 ኛው ጠቅላላ ጉባዔ ላይ የሚወክሉት ሰርጌ ላቭሮቭ በሀገራቸው ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት መስራት የጀመሩት በ22 ዓመታቸው ሲሆን በድምሩ ለግማሽ ክፍለ ዘመን (ለ 50 ዓመታት) አገልግለዋል።