ኢትዮጵያ፤ እንኳን ኤርትራን ከመሰለ ጎረቤቷ ጋር ይቅርና ከፈለገችው ሀገር ጋር የመተባበር መብት አላት“- አምባሳደር ዲና ሙፍቲ
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባዩ፤ አሁን ላይ ነጻ የውጭ ግንኙነት ማራመድን የማይወዱ አካላት አሉ ብለዋል
ኢትዮጵያ ከሀገሮች ጋር ባላት ግንኙነትና በሕዳሴ ግድብ ሰበብ ጫና እየተደረገባት ነውም ተብሏል
“ኢትዮጵያ እንኳን ከጎረቤት ሀገር ኤርትራ ጋር ይቅርና ከፈለገችው ሀገር ጋር በትብብር የመስራትና የማደግ መብቷን ምንም ሊነፍጋት እንደማይችል” የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።
የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ ቃል አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ከአል ዐይን ኒውስ ጋር በነበራቸው ቆይታ ኢትዮጵያ ከፈለገችው ሀገር ጋር የውጭ ግንኑነትን ማከናወን መብቷ መሆኑን ማንም ሊገነዘበው እንደሚገባ ተናግረዋል።
አሁን ላይ እየመጣ ያለው ጫናም ሀገሮችን የመግዛት አባዜ እንደሆነ የገለጹት ቃል አቀባዩ ፤ አንዳንድ አካላት ነጻ የውጭ ግንኙነት ማራመድን እንደማይወዱም ለአል ዐይን ተናግረዋል።
አንዳንድ ወገኖች በኢትዮጵያ ላይ ጫና የሚያደርጉት በሕዳሴ ግድብ እና ከሀገሮች ጋር ባላት ግንኙነት መሆኑንም አምባሳደር ዲና አንስተዋል።
አዲስ አበባ፤ ከሞቃዲሾ እና አስመራ ጋር የፈጠረችው ጥምረት ጫናው እንዲመጣ አድርጓል ወይ በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ ኢትጵያ ላይ ጫና የማድረጊያው አንዱ መንስኤ እንደሆነ ጠቅሰዋል። ይህ የሆነውም አንዳንድ በሚል ስማቸውን ያልገለጿቸው ወገኖች ሀገሮችን የመግዛት አባዜ ስላለባቸው መሆኑን አንስተዋል።
በዚህም መሰረት አንዳንድ አካላት ነጻ የውጭ ግንኙነት ማራመድን እንደማይወዱ ያነሱት ቃል አቀባዩ፤ የሀገሮችን ትብብር ሰፍሮ መስጠት የሚፈልጉ እንዳሉም ተናግረዋል።
በተለይም “ከዚህ ጋር ተገናኝ፤ ከዚህ ጋር አትገናኝ ፤ ከዚህ ጋር ሂድ፤ ከዚህ ጋር አትሂድ“ የሚል ትዕዛዝ መሰል መልዕክት የሚናገሩም እንዳሉ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ የምታካሂደውን የውጭ ግንኙነት ስራ የምታካሂደው በራሷ መብት መሆኑን የገለጹት አምባሳደር ዲና ይህንን የኢትዮጵያን መብት መከበር የማይፈልጉ ወገኖች በተለያየ መንገድ ጫና ለማድረግ መሞከራቸውን ገልጸዋል፡፡
ሌላኛው ኢትዮጵያ ላይ ጫና የማድረጊያው ስልት የሕዳሴ ግድብ መሆኑን የሚናገሩት ቃል አቀባዩ “የሕዳሴ ግድብን አጉል እንደሚጎዳቸው አድርገው የወሰዱ አሉ”ብለዋል።
ፕሮጀክቱን ያለ አግባብ በመረዳት እንደሚጎዳቸው አድርገው የወሰዱ አካላት መኖራቸውን የተናገሩት አምባሳደር ዲና ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ እየገነባችው ያለውን የሕዳሴ ግድብን “በእኛ ላይ የመጣ ነው“ በሚል እንደ ስጋት የሳሉ መኖራቸውን አስታውቀዋል።
በኢትዮጵያ ያለውን ሁኔታ በሚገባ ባለማወቅ አሊያም ሆነ ብሎ ጫና እየተደረገ መሆኑ በተደጋጋሚ በመንግስት በኩል ተገልጿል። ጫና የሚያደርጉ አካላትን በደፈናው ምዕራቡ ዓለም ብሎ ከማስቀመጥ ይልቅ አንዳንድ ወገኖች ቢባል እንደሚሻል ቃል አቀባዩ ተናግረዋል።
ይህም ከፖለቲከ፤ ከመንግስት እንዲሁም ከሚዲያ ሰዎች መሆኑን አምባሳደር ዲና ገልጸዋል።
ባለማወቅ ኢትዮጵያ ላይ ጫና ለማድረግ የሚሞክሩ ኃይሎች “የውሸት ወሬ የሚያሰራጨውን ኃይል“ ማንነት እየተደረዱ የሚሄዱበት ዕድሉ ከፍተኛ እንደሆነና አሁንም እየተረዱትም እንደሆነ ቃል አቀባዩ ገልጸዋል። “ውሸት ሚሲራጨው ኃይል ራቁቱን ሲቀር ዕውነታው ሲገለጽ ኢትዮጵያ ወደፊት ትሄዳለች“ ብለዋል።