የሩሲያ ጦር ከምስራቃዊቷ የዩክሬን ከተማ የመጨረሻ መውጫ የሆነውን ድልድይ ማውደሙ ተገለጸ
ሩሲያ የዶንባስ ክልል ነጻ እስከሚወጣ ጦርነቱ እንደማይቆም መግለጿ ይታወሳል
የክልሉ አስተዳዳሪ 70 በመቶ የሚሆነው የሲቪዬሮዶኔትስክ ከተማ በሩሲያ ጦር ቁጥጥር ስር ውሏል
የሩሲያ ጦር በምስራቅ ዩክሬን ከምትገኘው የሲቪዬሮዶኔትስክ ከተማ መውጫ የሆኑ መንገዶችን መቁረጡን የዩክሬን ባለስልጣናት መናገራቸውን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ታሪካዊ የይገባኛል ጥያቄ ያላት ሩሲያ በዶንባስ ግዛት ድል ለመቀዳጀት በመግፋት ላይ ትገኛለች፡፡ከከተማዋ የሚያስወጣው የመጨረሻው ድልድይ በመሰበሩ ምክንያት በከተማው የቀሩ ሰላማዊ ዜጎች መውጣት ከማይችሉበት ደረጃ መድረሳቸውን የክልሉ አስተዳዳሪ ተናግረዋል፡፡
አስተዳዳሪው እንዳሉት ከሆኑ በአሁኑ ሰአት 70 በመቶ የሚሆነው የከተማዋ ክፍል በሩሲያ ቁጥጥር ስር ውሏል፡፡
ዩክሬን ሲቪዬሮዶኔትስክን ለመከላከል ተጨማሪ ከባድ የጦር መሳሪያዎች እርዳታ እንዲለግሷት ምእራባውያንን ጠይቃለች፡፡ ዩክሬን በምስራቅ ዩክሬን የሚካሄደው ጦርነት አራት ወር ባስቆጠረው ጦርነት አቅጣጫ ሊያስቀይር የሚችል ቁልፍ ፍልሚያ ነው ብላለች፡፡
ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘለንስኪ እንዳሉት በምስራቅ ዶንባስ ክልል የሚደረገው ጦርነት በአውሮፓ ታሪክ ውስጥ እጅግ በጣም ጭካኔ የተሞላበት ተደርጎ ይወርዳል። የሉሃንስክ እና የዶኔትስክ ግዛቶችን ያቀፈው የዶምባስ ክልል በሩሲያ ተገንጣይ ኃይሎች የይገባኛል ጥያቄ ቀርቦበታል፡፡
ሩሲያ በላፈው የካቲት ወር በዩክሬን ላይ ልዩ ያለችውን ወታደራዊ ጥቃት የከፈተችው ምእራባውያን ዩክሬንን የኔቶ አባል ለማድግ እየተንቀሳቀሱ ነው፤ይህም ለደህንነቴ ያሰጋኛል በሚል ነበር፡፡
አሜሪካን ጨምሮ ምእራባውያን ሀገራት ሩሲያ ያዳክማል ብለው ያሰቡትን ሁሉ ማእቀብ ጥለዋል፤እየጣሉም ይገኛሉ፡፡
ሩሲያ ወዳጅ አይደሉም ያለቻቸው ምእራባውያን ሀገራት ነዳጇን በሩብል እንዲገዙ በማድረግ የተጣለባትን ማእቀብ ለመበቀል ሞክራለች፤ በዚህም የተወሰኑ የአውሮፓ ሀገራት በሩሲያ ፍላጎት ነጃጅ እየገዙ ነው፡፡
የአውሮፓ ህብረትም የነዳጅ ገዥ ኩባንያዎች በሩሲያ ላይ የተጣለውን ማእቀብ በማይጻረር ምልኩ ነዳጅ በሩብል ምዛት ይችላሉ ማለቱም ይታወሳል፡፡
ጦርነቱ አሁንም በመካሄድ ላይ ሲሆን ሩሲያ የዶምባስ ግዛት ነጻ እስከሚወጣ ድረስ ይቀጥላል ብላለች፡፡