ዩክሬን በህዝብ ተወዳጅ ናቸው የተባሉ ሁለት ሚኒስትሮችን ከስልጣን አነሳች
ከሀላፊነት የተነሱት ሚኒስትሮች የዩክሬን አህል ምርቶች ለዓለም ገበያ እንዲቀርቡ ስኬታማ ነበሩ ተብሏል
የቀድሞው የዩክሬን ጦር አዛዥ በጤና ምክንያት በሚል ከጦሩ እንዲወጡም አድርጋለች
ዩክሬን በህዝብ ተወዳጅ ናቸው የተባሉ ሁለት ሚኒስትሮችን ከስልጣን አነሳች፡፡
የዩክሬን ህግ አውጪ ምክር ቤት የሀገሪቱን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስር እና የግብርና ሚኒስትሮች ከሀላፊነት እንዲነሱ በአብላጫ ድምጽ ወስኗል፡፡
ከስልጣን የተነሱት ሁለቱ ሚኒስትሮች ሩሲያ የዩክሬን ስንዴ እና ጥራጥሬዎች በጥቁር ባህር በኩል እንዳይጓዙ እገዳ ስትጥል በቱርክ እና ተመድ በኩል ድርድሮች እንዲካሄዱ ያደረጉ እንደነበሩ ተገልጿል፡፡
ሚኒስትሮቹ ዩክሬን በጦርነት ውስጥ ሆና ኢኮኖሚዋ ወደ ከፋ ሁኔታ እንዳይገባ የተለያዩ ጥረቶችን ሲያደርጉ የነበሩ በህዝብም ያላቸው ተቀባይነት ጥሩ እንደነበሩ ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ከስልጣን ከተነሱት ውስጥ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር የሆኑት ኦሌክሳንደር ኩብራኮቭ “ከስልጣን እንደምነሳ አስቀድሞ የነገረኝ አካል ማንም አልነበረም፣ የፓርላማ አባላትም በእኔ ላይ ድምጽ ሲሰጡ ለእኔ እድል አልተሰጠኝም፣ ድምጽ ከመሰጠቱ በፊት ራሴን እንድከላከል እድል ሊሰጠኝ ይገባ ነበር ” ነበር ሲሉ በፌስቡክ ገጻቸው ላይ ጽፈዋል፡፡
ሩሲያ ወደ ዩክሬን የገቡ የፈረንሳይ ወታደሮችን እንደምትመታ ዛተች
የሚኒስትሮቹ ከስልጣን መነሳት የዩክሬንን ሚኒስትሮች ለሁለት እንደከፈለ የተገለጸ ሲሆን በተለይም ሩሲያ በምታደርሳቸው የኢኮኖሚ ጥቃቶች ምክንያት የሀገሪቱ ኢኮኖሚ ልዩ ትኩረት የሚፈልግበት ወቅት መሆኑ በሚኒስሮቹ መነሳት ቅሬታ መፈጠሩ በዘገባው ላይ ተጠቅሷል፡፡
ዩክሬን ላለፉት ሁለት ዓመት የዩክሬን ጦር አዛዥ የነበሩት ጀነራል ቫለሪ ዛሉዝኒን ከሀላፊነት በማንሳት በብሪታንያ የዩክሬን አምባሳደር አድርገው ሾመዋል፡፡
እንዲሁም ፕሬዝዳንት ቮሎዶሚር ዘለንስኪ የመንግስት ጥበቃ ሃላፊ የሆኑት ሰሪ ሩድን ከሃላፊነት ያነሱ ሲሆን በዚህ ጥበቃ ቡድን ስር ያሉ ሁለት ወታደሮች ከሰሞኑ በፕሬዝዳንቱ ላይ ግድያ ሊፈጽሙ ሲያሴሩ መያዛቸው ለእርምጃው በምክንያትነት ተጠቅሷል፡፡