ሩሲያውያን ያላቸውን ዶላርና ዩሮ በቻይና ዩዋን እየለወጡ ነው ተባለ
የሩሲያ ኩባንያዎች ዩዋን መጠቀማቸው ከምእራባውያን ማእቀቦች ለማምለጥ እንደሚያግዛቸው ተገልጿል
ቻይና ለሩሲያ ዓለም አቀፍ ግብይቶች አመራጭ ሆናለች
ሩሲያውያን በእጃቸው ላይ ያለ የአሜሪካ ዶላር እና የአውሮፓ ዩሮ ገንዘቦችን በቻይና ዩዋን እየለወጡ ነው መሆኑ ተገለፀ።
የፋይናንሻል ጉዳዮችን የሚያጠናው የሩሲያው ኮማርሳንት ኩባንያ ባወጣው መረጃ፤ በባለፈው ወር ብቻ ፤በሩስያ ባንኮች የተመዘገቡ አዳዲስ የዩዋን የሂሳብ ደብተሮች (አካውንቶች) ጭማሪ አሰይቷል።
ጥናቱ፤ የሩስያ ዜጎች የውጭ ምንዛሪ ቁጠባቸውን ወደ ቻይናው ዩዋን በመቀየር ላይ ናቸውም ብለዋል።
ለምሳሌ በቲንኮፍ ባንክ በዩዋን የተያዘው የገንዘብ መጠን ስምንት እጥፍ ማደጉንና፤ ባንክ ሴንት ፒተርስበርግ ደግሞ የ3 ነጥብ 5 እጥፍ እድገት ማሳየቱን ጥናቱ አመላክቷል።
ከዚህም በተጨማሪ ፤ ብዙ ኩባንያዎች ግብይታቸውን በዩዋን እያደረጉ ነው ያለው ጥናቱ፤ የሩሲያ የነዳጅ ኩባንያዎች፣ የከሰል ማዕድን አምራቾች እና የብረታ ብረት አምራቾች ወደ ዩዋን ሰፈር መሸጋገር መጀመራቸውን ተገልጿል።
አሁን ላይ በሞስኮ ከቻይናው ምንዛሬ ዩዋን ጋር የተደረጉ ግብይቶች በጣም እንደጨመሩ ያስታወቀው ጥናቱ ፤ በዚህ ሳምንት ብቻ 230 ሚሊየን ዶላር ገደማ የገንዝብ ልውውጥ ተደርጓልም ብለዋል።
የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች፤ የሩሲያ ኩባንያዎች እየሄዱበት ያለው መንገድ የዶላር እና ዩሮ መዳረሻን ከመገደቡ በተጨማሪ ከምእራባውን ማእቀቦች ለማምለጥ ሚያስችያስችል ሁነኛ ዘዴ ነው ብለውታል።
ምእራባውያን በሩሲያ ላይ ማእቀብ ቢጥሉም ፤ ማእቀቡን ያልተቀላቀለችውና ብሄራዊ ገንዘቧን ክፍት አድርጋለች የቆየችው ቻይና አሁን ላይ ለሩሲያ ዓለም አቀፍ ግብይቶች አመራጭ እንደሆነችም ነው ባለሙያዎቹ የሚናገሩት።
ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይ ኤም ኤፍ) በሩሲያ ላይ የተጣሉ የገንዘብ ማዕቀቦች የዶላርን ተፅዕኖ ፈጣሪነት ሊቀንሱት እንደሚችሉ ማሳሰቡ ይታወሳል
የድርጅቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ጊታ ጎፒናዝ አሁን ላይ አሜሪካን ጨምሮ የተለያያ ወገኖች በሞስኮ ላይ የጣሏቸው ማዕቀቦች የዓለምን የገንዘብ ሥርዓት የተበታተነ ሊያርገው እንደሚችል ገልጸው ነበር።