በዩክሬን ጦርነትና በሌሎች ተያያዥ ምክንያቶች ሩሲያዊያን በፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ላይ ያላቸው እምነት ጨምሯል
75 በመቶ ሩሲያዊያን በፕሬዝዳንት ፑቲን ላይ እምነት እንዳላቸው ገለጹ።
ሩሲያን ከፈረንጆቹ 1999 ጀምሮ በፕሬዝዳንትነት እየመሩ ያሉት ቭላድሚር ፑቲን በሀገሬው አሁን ላይ በህዝብ ያላቸው ተቀባይነት መጨመሩ ተገልጿል።
የህዝብ ጥናት ፋውንዴሽን ባስጠናው ጥናት መሰረት 75 በመቶ ሩሲያዊያን በፕሬዝዳንት ፑቲን ይተማመናሉ።
በጥናቱ ከተሳተፉት ውስጥ 13 በመቶዎቹ በፕሬዝዳንት ፑቲን ላይ እምነት እንደሌላቸው ሲገልጹ 12 በመቶዎቹ ደግሞ አቋም እንዳልያዙ ተናግረዋል ተብሏል።
ሩሲያ ከዩክሬን ጋር ወደ ጦርነት ማምራቷን ተከትሎ ከምዕራባዊያን ሀገራት ከ12 ሺህ በላይ ማዕቀቦች ተጥሎባታል።
የማዕቀቦቹ ዓላም የሩሲያን ኢኮኖሚ ሲጎዳ ህዝብ እንደሚያምጽ እና የፕሬዝዳንት ፑቲን ተቀባይነት እንዲቀንስ ማድረግ ያለመ ነበር።
ይሁንና ፕሬዝዳንት ፑቲን የንግድ አድማሳቸውን ከአውሮፓ ይልቅ ወደ እስያ፣ ላቲን እና አፍሪካ በማድርጓ ኢኮኖሚዋን ከድቀት መታደጓ ተገልጿል።
ከዩክሬን ጋር የገባችበትን ጦርነት ከሩሲያ ግዛቶች ውጪ በማድረግ የጦርነቱን ጉዳት መቀነስ ተችሏልም ተብሏል።
18 ወራት የዘለቀው የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት አሁንም የቀጠለ ሲሆን በተለይም ዩክሬን ከምዕራባዊያን ሀገራት ያገኘቻቸው የጦር መሳሪያዎች በሩሲያ ላይ የተለየ ድል ሊያቀዳጃት እንዳልተቻለም ተገልጿል።
በነዚህ እና በሌሎች ተያያዥ ምክንያቶች ሩሲያዊያን በፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ላይ ያላቸው እምነት መጨመሩን ስፑትኒክ ዘግቧል።