ፕሬዝዳንቱ ጊዜ እየገዙ እንጂ የቨግኒ ፕሪጎዥን መቀጣታቸው እማይቀር ነው ስትል አሜሪካ ገልጻለች
ፕሬዝዳንት ፑቲን በቀለኛ ሰው መሆናቸውን አሜሪካ ገለጸች።
የሩሲያው ቅጥረኛ ተዋጊ ቡድን ዋግነር ከአንድ ወር በፊት የሀገሪቱ ጦር ጥቃት ከፈተብኝ በሚል በጦሩ ላይ አምጾ እንደነበር ይታወሳል።
የዋግነርን አመጽ ተከትሎም በቡድኑ አዛዥ የቨግኒ ፕሪጎዚን ላይ የእስር ማዘዣ ከመውጣቱ በተጨማሪም በሀገር ክህደት ወንጀል ክስ ተመስርቶባቸውም ነበር።
ይሁንና የቤላሩሱ ፕሬዝዳንት አሌክሳንደር ሌኬሾንኮ ባደረጉት ሽምግልና ፕሪጎዥን አመጹ ቆሞ ወደ ቤላሩስ እንዲኮበልል የተመሰረተበትም ክስ እንዲቋረጥ ተደርጓል።
የአሜሪካ የስለላ ተቋም ሲአይኤ ሀላፊ ዊሊያም በርንስ በጉዳዩ ዙሪያ እንዳሉት "ፕሬዝዳንት ፑቲን በቀለኛ ሰው ናቸው" ሲሉ መናገራቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።
በርንስ አክለውም ፕሬዝዳንት ፑቲን ትክክለኛውን ጊዜ እየጠበቁ እንጂ የዋግነሩ አዛዥ ፕሪጎዥን ለፈጸመው ስህተት መቀጣቱ አይቀሬ እንደሆነም ተናግረዋል።
የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ከሰሞኑ "የዋግነሩ አለቃ ተመርዘው ሊገደሉ ይችላሉ" ሲሉ መናገራቸው ይታወሳል።
በተመሳሳይ ጉዳይ ላይ ለሚዲያዎች የተናገሩት ዊሊያም በርንስም "እኔ ፕሪጎዥን ብሆን ምግብ ቀማሼን አባርራለሁ" ብለዋል።
የዋግነር አመጽ በፕሬዝዳንት ፑቲን ስልጣን እና ህልውና ላይ የተቃጣ ቀጥተኛ ጥቃት ነው ያሉት በርንስ ጉዳዩ በዚሁ ያበቃል ብለው እንደማያስቡም ተናግረዋል ።
ፕሬዝዳንት ፑቲን ከዩክሬን ጋር የገቡበት ጦርነት በቀላሉ የሚወጡት ጉዳይ እንዳልሆነላቸው የተናገሩት የሲአይኤው ሀላፊ ሞስኮ በመጨረሻም ያቀደችውን ድል አታስመዘግብም ሲሉም ገልጸዋል።