ሩሲያ አውሮፓንና አሜሪካን በሀይፐርሶኒክ ሚሳኤል ልትመታ እንደምትችል አስጠነቀቀች
የቀድሞ የአሜሪካ የጦር ጀነራል ኔቶ የሩሲያን ጦር በቀላሉ ማውደም እንደሚችል ተናግረዋል
ዶንምባስ እና ሌሎች ግዛቶች በህዝበ ውሳኔ ወደ ሩሲያ መካለላቸው እንደማይቀር ሩሲያ አስታውቃለች
ሩሲያ አውሮፓን እና አሜሪካን በሀይፐርሶኒክ ሚሳኤል ልትመታ እንደምትችል አስጠነቀቀች።
ሰባት ወራትን ያስቆጠረው የሩሲያ ዩክሬን ጦርነት አሁን ደግሞ አዳዲስ ክስተቶችን ወደ ማስተናገድ በመሸጋገር ላይ ይገኛል።
በአሜሪካ እና ምዕራባዊያን የጦር መሳሪያ እርዳታ በመታገዝ ዩክሬን በሩሲያ የተያዙ ግዛቶችን በማስለቀቅ ላይ ስትሆን ሩሲያ ደግሞ አራት የዩክሬን ግዛቶችን ወደ ራሷ ለመጠቅለል ከዛሬ ጀምሮ ህዝበ ውሳኔ ታካሂዳለች።
ለዚህ ተልዕኮዋ እንዲረዳትም 300 ሺህ ተጠባባቂ ጦሯን የጠራችው ሩሲያ ብሄራዊ ደህንነቷ ስጋት ውስጥ ከገባ ደግሞ የኑክሌር ጦሯን ጨምሮ ማንኛውንም መንገድ እንደምትጠቀም ፕሬዝዳንት ፑቲን ተናግረዋል።
የሩሲያን አዲስ ውሳኔ ተከትሎ አሜሪካ፣ የአውሮፓ ህብረት እና ኔቶ በጉዳዩ ዙሪያ ምላሽ በመስጠት ላይ ሲሆኑ በአውሮፓ የተሰማራው የቀድሞው የአሜሪካ ጦር ጀነራል ቤን ሆጅስ ሩሲያ የምትመካበትን ጦር ኔቶ ማውደም ይችላል ብለዋል።
ሩሲያ በዩክሬን ኑክሌር ጦር ከተጠቀመች ሞስኮ የምትመካበት እና በጥቁር ባህር ላይ ያሰፈረችው ጦር አውሮፓ ያለው የአሜሪካ ጦር ሊያወድመው ይችላል ሲሉ ተናግረዋል።
የሩሲያ የቀድሞ ፕሬዝዳንት እና የአሁኑ የሀገሪቱ ምክትል የጸጥታ ሀላፊ ለአሜሪካው የጦር ጀነራል አስተያየት ምላሽ ሰጥተዋል።
ሩሲያ ሀይፐር ሶኒክ በተሰኘው ሚሳኤል ብቻ የአወውሮፓ እና አሜሪካ ከተሞችን ልትመታ እንደምትችል አስጠንቅቀዋል ሲል ራሺያን ቱዴይ ዘግቧል።
ሩሲያ ለአውሮፓ እና አሜሪካ ምላሽ ተጠባባቂ ጦሯን ብቻ ሳይሆን ስትራቴጂክ የኑክሌር ጦር መሳሪያዎቿንም ጥቅም ላይ ልታውል ትችላለች ብለዋል።
ሉሃንስክ እና ዶንብአስ ግዛቶችን ጨምሮ በሌሎች የሩሲያ ጦር በተቆጣጠራቸው ቦታዎች በህዝበ ውሳኔ ወደ ሩሲያ መጠቃለላቸው አይቀሬ መሆኑንም ድሚትሪ ሜድቬዴቭ ተናግረዋል።
የሩሲያ ሀይፐርሶኒክ ሚሳኤሎች በአውሮፓ እና አሜሪካ ያሉ ታርጌቶችን በፍጥነት እንደሚመቱ እርግጠኞች ነን ያሉት ሜድቬዴቭ ሩሲያ የራሷን መንገድ እንደምትከተል የምዕራባዊያን ዜጎች ሊረዱ ይገባል ማለታቸውን ዘገባው ላይ ተጠቅሷል።
ሩሲያ ባለፉት ቀናት ውስጥ 100 ሺህ ጦር ወደ ዩክሬን ድንበሮች አስጠግታለች የተባለ ሲሆን ኔቶ በበኩሉ ተጨማሪ ስምንት ሺህ ጦር ወደ ባልቲክ ሀገራት መላኩ ተጠቅሷል።