ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በዋግነር ጦር አዛዥ ፕሪጎዚን ላይ የተመሰረተው ክስ ውድ መደረጉ ተገልጿል
የሩሲያ ቅጥረኛ ወታደር አዛዥ የሆኑት ፕሪጎዚን እና ጦራቸው በሩሲያ ጦር የአየር ላይ ጥቃት ተፈጸመበት በሚል በትናንትናው ዕለት ማመጻቸው ይታወሳል።
በደቡባዊ ሩሲያ ባሉ አካባቢዎች የዋግነር ጦር አባላት ወደ ሩስቶቭ እና አካባቢዋ በመግባት የመንግስት ተቋማትን መቆጣጠር ጀምረውም ነበር።
በዋግነር ጦር ድርጊት የተበሳጩት የሩሲያ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲንም ጉዳዩ የሀገር ክህደት መሆኑን ተናግረው በፕሪጎዚን ላይም የእስር ትዕዛዝ አስተላልፈው ነበር።
የቤላሩሱ ፕሬዝዳንት አሌክሳንደር ሎካሼንኮ ከዋግነር ቅጥረኛ ጦር አዛዥ ይቨግኒ ፕሪጎዚንን እና ፕሬዝዳንት ፑቲንን በማወወየት መፍትሄ መገኘቱ ተገልጿል።
በዚህ ስምምነት መሰረት ፕሪጎዚን እና ጦራቸው ተኩስ በማቆም ወደ ቀድሞ ካምፓቸው ይመለሳሉ የተባለ ሲሆን ወታደሮቹ ትናንት ተቆጣጥረዋት ከነበረችው ሩስቶቭ ከተማ ለቀው ወጥተዋል ሲል አርቲ ዘግቧል።
የእስር ማዘዣ የወጣባቸው የዋግነሩ አዛዥ ፕሪጎዚን ደግኖ ወደ ቤላሩስ የሚጓዙ ሲሆን የተመሰረተባቸው የሀገር ክህደት ክስም መቋረጡ ተገልጿል።
ከ50 ሺህ በላይ ይሆናሉ የተባሉት የዋግነር ቅጥረኛ ወታደሮች ደግሞ ከሩሲያ መከላከያ ጋር አዲስ የስራ ስምምነት እንደሚፈጽሙ ተገልጿል።
ይህ በዚህ እንዳለም አሜሪካ ዋግነር ቅጥረኛ ወታደራዊ ቡድንን በሽብርተኝነት ለመፈረጅ የያዘችውን እንቅስቃሴ ለጊዜው ማቋረጧን አስታውቃለች።
አሜሪካ ከዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰችው ከሩሲያ መከላከያ ጋር ግጭት ውስጥ የገባው ዋግነር በሽብርተኝነት ቢፈረጅ ከፕሬዝዳንት ፑቲን ጋር ያለውን ግንኙነት ሊያጠብቅ ይችላል በሚል ነው ተብሏል።