"ኤስ-500" የሩሲያ ሃይፐርሶኒክና ፀረ-ኒውክሌር የአየር መከላከያ ስርዓት
"ኤስ-500" ምንኛውንም ሃይፐርሶኒክ ሚሳዔልና የጦር አውሮፕላን በአየር ላይ ማውደም የሚችል ነው
ፕሬዝዳነት ፑቲን ሩሲያ “ፕሮሜቴየስ” የተባለውን ይሀንን መሳሪያ ለውጊያ ታሰማራለች ብለዋል
የሩሲያው ፕሬዝዳነት ቭላድሚር ፑቲን ሀገራቸው “ኤስ-500” “ፕሮሜቴየስ” የተባለውን ሃይፐርሶኒክ እና ፀረ-ኒውክሌር የአየር መከላከያ ስርዓት ለውጊያ እንደምታሰማራ አስታውቃለች።
ፕሬዝዳንት ፑቲን ይህንን ያስታወቁት በሞስኮ ወታደራዊ ኮሌጅ የሰልጣኖች የምረቃ በዓል ላይ ባደረጉት ንግግር መሆኑን ዘ ሰን ዘግቧል።
ሩሲያ ቅድሚያ በምትሰጣቸው አካባቢዎች ላይ ያሏትን ትላልቅ መሳሪያ ታሰማራለች ያሉት ፕሬዝዳንቱ፤ ይህም የጦራቸውን እና የባህር ኃይላቸውን የውጊያ አቅም የበለጠ የሚያሳድጉ ናቸው ብለዋል።
ፕሬዝዳንት ፑቲን እንደምታሰማራቸው ካስታወቁት መሳሪያዎች ውስጥም “ኤስ-500” የሃይፐርሶኒክና ፀረ-ኒውክሌር የአየር መከላከያ ስርዓት አንዱ ነው።
“ኤስ-500” የአየር መከላከያ ስርዓት ሚሳዔል ሲሆን፤ ማንኛውንም ከጠላት የተወነጨፉ ሚሳዔሎችን እና የጠላት አውሮፕላኖችን በ200 ኪሎ ሜትር ከፍታ ላይ እያለ ማውደም የሚችል ነው።
የሩሲያ አየር ኃይል አዛዥ ሜጀር ጄነራል ሰርጊ ባባኮቭ፤ “ኤስ-500” የአየር መከላከያ ስርዓት ስርዓት የአዲሱ ትውልድ የፀረ አውሮፕላን ስርዓት መሆኑን የገለፁ ሲሆን፤ የባላስቲክ ሚሳዔሎችን እና የአህጉር አቋራጭ ሚሳዔችን አየር ላይ እያለ ማውደም የሚችል ነው ብለዋል።
እንዲሁም “ኤስ-500” የአየር መከላከያ ስርዓት ሃይፐርሶኒክ አውሮፕላኖችን እና ደሮኖችን መትቶ መጣል የሚችል መሆኑን አስታውቀዋል።
አዲሱ የሩሲያ “ኤስ-500” የአየር መከላከያ ስርዓት የባላስቲክ ሚሳዔልን በ600 ኪሎ ሜትር ላይ እንዲሁም የጦር አውሮፕላኖችን በ500 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ምትቶ የማውደም አቅም አለው ተብሏል።