ሳዑዲ አረቢያ በኢትዮጵያ ውጊያ ላይ ያሉ ኃይሎች ጦርነት እንዲያቆሙ ጠየቀች
ኦሊሰጉን ኦባሳንጆ ግጭቱን በሰላማዊ መንገድ እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውን መግለጻቸው ይታወሳል

በኢትዮጵያ ጦርነት ላይ ያሉ ወገኖች ውጊያውን እንዲያቆሙ የሳዑዲ አረቢያ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ጥሪ አቀረበ
የሳዑዲ አረቢያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ትናንት ምሽት ባወጣው መግለጫ በውጊያ ለይ ያሉ ወገኖች የተኩስ አቁም እንዲያደርጉና ጦርነቱን እንዲያቆሙ ጥሪ አቅርቧል፡፡
ሪያድ በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለውን ጦርነትና አጠቃላይ አዳዲስ ጉዳዮችን እየተከታተለች መሆኑንም ገልጻለች፡፡ አሁን ያለው ጦርነትና ወጊያ ቆሞ ድርድር መደረግ እንዳለበት የገለጸችው ሳዑዲ ሁኔታዎቹን ማጋጋል እንደማያስፈልግም ጠይቃለች፡፡
እየተካሄደ ያለው ጦርነት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ሰላማዊ መፍትሄዎች መፈለግ እንደሚገባም የሳዑዲ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ጠይቋል፡፡ ንጹሃን እንዳይጎዱና ረዲኤት ድርጅቶች ገብተው እንዲሰሩ መደረግ እንዳለበትም ሪያድ ገልጻለች፡፡
በፌደራል መንግስት እና የትግራይ ክልልን ሲያስተዳድር በነበረው ህወሓት መካከል አለመግባባት የተፈጠረው፤ ኢትዮጵያን ለ27 አመታት ሲያስተዳድር የነበረው የገዥ ፓርቲ ግንባሮች በመዋሃድ ብልጽግና ፓርቲን ሲመሰርቱ ህወሓት የውህደቱ አካል አልሆንም ብሎ በማፈንገጡ ነው።
ህወሓት የፌደራል መንግስቱ ህገወጥ ነው ያለውን ምርጫ ማካሄዱም የአልመግባባቱ ጡዘት ውጤት ነበር።
በሁለቱ አካላት መካከል የነበረው አለመግባባት ወደ ወታራዊ ግጭት ያመራው፤ ጥቅምት 24፣2013ዓ.ም ህወሓት በትግራይ ክልል በሚገኘው የሰሜን እዝ ላይ ጥቃት ማድረሱን ተከትሎ ነበር፡፡
ክህደት ፈጽሟል ባለው ህወሓት ላይ “የህግ ማስከበር ዘመቻ” በማወጅ የትግራይ ዋና ከተማና ብዙ ቦታዎችን መያዝ የቻለው መንግስት ከ8 ወራት በኋላ ለትግራይ ህዝብ የጽሞና ግዜ ለመስጠት በማሰብ ከትግራይ ክልል ሰራዊቱን ማስወጣቱ ይታወሳል። በክልሉ በነበረው ጦርነት ወቅት ዜጎች መፈናቃላቸውንና መገደላቸውን ኢሰመኮና ሌሎች አለምአቀፍ ተቋማት መግለጻቸው ይታወሳል፡፡
መንግስት ጦሩን ከክልሉ ማስወጣቱን ተከትሎ፣ ሕወሓት ወደ አማራ አፋር ክልል በመግባት ጥቃት በመሰንዘር፤ ሰዎች እንዲገደሉና በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች እንዲፈናቀሉ ማድረጉን መንግስት ገልጿል። አሁን ጦርነት ባለባቸው የአማራ ክልል አካባቢዎች ህዝብ ለርሃብና ለሞት አደጋ የተዳረገ ሲሆን እስካሁን ከ 2 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ጦርንቱን ሸሽተው መፈናቀላቸውን የአማራ ክልል መንግስት ገልጿል፡፡
በኢትዮጵያ መንግስት በሽብር የተፈረጀው ህወሓት ደቅኖታል ያለውን ሉአላዊነትን ችግር ውስጥ የሚያስገባ አደጋ ለመቀልበስ ባለፈው ሳምንት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጇል።
በአፍካ ህብረት የአፍሪካ ቀንድ ከፍተኛ ተወካይ ኦሊሰጉን ኦባሳንጆ፣ በኢትዮጵያ አንድ አመት ያስቆጠረውን ግጭት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውን መግለጻቸው ይታወሳል፡፡