በአዲስ አበባ ኢድ ሶላት ላይ በተነሳው ረብሻ በፀጥታ ኃይሎችና በንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን መንግስት አስታወቀ
በአብዛኞቹ የሀገሪቱ አካባቢዎች የ1443ኛው ኢድ አልፈጥር በዓል ሶላት በሰላም ተጠናቋል
የአዲስ አበባ ፖሊስ “የረብሻውን መነሻና ከዚህ ጋር ተያያዥነት ያላቸውን ሌሎች ጉዳዮችን ለህዝብ አሳውቃለሁ” ብሏል
በአዲስ አበባ ከተማ በኢድ ሶላት ላይ በተነሳው ረብሻ በፀጥታ ሃይሎችና በንብረት ላይ መጠነኛ ጉዳት መድረሱን መንግስት አስታወቀ።
የኢትዮጵያ መንግስት የኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ባወጣው መግለጫ፤ በዛሬ በአዲስ አበባ የታላቁ ዒድ ሶላት ላይ “ሁከትና ብጥብጥ” እንዲፈጠር ሙከራ መደረጉን አስታውቋል።
በዚህም በተፈጠረው ረብሻ “በሰማዕታት ኃውልት እና በመስቀል አደባባይ በንብረት እንዲሁምበፀጥታ ሃይሎች ላይ መለስተኛ ጉዳት ደርሷል” ያለው መንግስት፤ “በሰላም ወዳድ አማኞችና በፀጥታ ኃይሎች ቅንጅት የትርምስ ፍላጎቱና ዕቅዱ ከሽፏል” ብሏል።
“አብዛኛዉ ሰላም ወዳድ የእምነቱ ተከታዮች በዓሉ በተረጋጋና በሰከነ ሁኔታ እንዲካሄድ ያደረጉት ተሳትፎና ከፀጥታ አካላት ጋር አብሮ ለመስራት ያሳዩት ተነሳሽነት በእጅጉ የሚደነቅና የሚበረታታ ነው” ብሏል በመግለጫው።
መግለጫው አክሎም “የውስጥ ባንዳዎች በሃይማኖት ሽፋን ከውጭ ኃይሎችና ከታሪካዊ ጠላቶች ጋር ተቀናጅተው ማህበራዊ ትስስሮቻችንን ለመበጣጠስ፤ በሀገራችን ውስጥ አስተማማኝ ሰላምና መረጋጋት እንዳይሰፍን ለማድረግ አልመው እየሰሩ ይገኛሉ” ብሏል።
በማህበራዊ ሚዲያዎች ሰሞኑን የፀረ-ኢትዮጵያ አቋሞቻቸውን በመግለፅ ቀጣይ ሊፈጥሩት ስላሰቡት ሁከት በአደባባይ ሲገልፁ መሰንበታቸውንም አስታውሷል።
በዛሬም በአዲስ አበባ የታላቁ ዒድ ሶላት ላይ የተደረገው ሙከራም የዚሁ እኩይ አላማ አካል እንደሆነም ነው በመግለጫው ያስታወቀው።
“መንግስት በፅንፈኞች ላይ የሚወስደውን እርምጃም አጠናክሮ ይቀጥላል” ያለው መግለጫው፤ ይህንን ተግባር ለማፈፀም መንግስት ሙሉ ቁርጠኝነትና ጠንካራ አቅም እንደላውም አረጋግጧል።
በአዲስ አበባ ከተፈጠረው ረብሻ ውጪ፤ በአብዛኞቹ የሀገሪቱ አካባቢዎች የ1443ኛው ኢድ አልፈጥር በዓል ሶላት በደማቅ ሁኔታ በመካሄድ በሰላም መጠናቀቁን የመንግስት የኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት አስታውቋል።
በተያያዘ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ባወጣው መግለጫ፤ በአዲስ አበባ በዛሬው ዕለት በተከበረው በ1 ሺህ 443ኛው የኢድ አልፈጥር በዓል የኢድ ሶላት ላይ ጥቂት ግለሰቦች ባስነሱት ረብሻ በንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን አስታውቋል።
በቀጣይ የረብሻውን መነሻና ከዚህ ጋር ተያያዥነት ያላቸውን ሌሎች ጉዳዮችን ለህዝብ እንደሚያሳውቅ ፖሊስ ጨምሮ ገልጿል።
በአዲስ አበባ የኢድ ሶላት ላይ በተፈጠረው ረብሻ በርካታ ወላጆች እና ልጆች መጠፋፋታቸውን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፤ በተለያዩ ማህበራዊ ትስስር ገጾች ላይም ወላጆች የጠፉባቸውን ልጆቻቸውን የሚያገኙበት ስፍራ እየተጠቆመ ተመልክተናል።