የሽግግር መንግሥት እንመሠርታለን በሚል በሚንቀሳቀሱ አካላት ላይ የጸጥታ አካላት አስፈላጊውን እርምጃ እንዲወስዱ ታዘዘ
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ዕዝ አራት ትእዛዞችን አስተላልፏል
የጦር ሜዳ ውሎዎችንና ውጤቶችን በተመለከተ፣ በዕዙ ሥልጣን ከተሰጠው አካል ውጪ ማሰራጨት ተከልክሏል
ማንኛውም ወታደራዊ እንቅስቃሴዎችን፣ የጦር ሜዳ ውሎዎችንና ውጤቶችን በተመለከተ፣ በዕዙ ሥልጣን ከተሰጠው አካል ውጪ ማሰራጨት ተከልክሏ
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ዕዝ ዛሬ ማምሻውን ተሰብስቦ፣ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የተመለከቱ ወቅታዊ ሁኔታዎችን ገምግሟል።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከተያዘለት ዓላማ አኳያ አፈጻጸሙ በመልካም ሁኔታ እየተከናወነ መሆኑን አረጋግጧል።
በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የተጀመሩ ሥራዎችን ለማጠናከርና ዕንቅፋት የሚሆኑትን ችግሮች ለማስወገድ አራት ትእዛዞች አስተላልፏል።
ከእነዚህም አንዱ ከሕግና ሥርዓት ውጭ የመለዮ ለባሾችን ዩኒፎርም ለብሶ መገኘት የተልእኮ አፈጻጸሙን እያወከ ይገኛል ያለው እዙ፣ በመሆኑም በማንኛውም ሁኔታ፣ ቦታና ጊዜ የመከላከያ ሠራዊትን፣ የፌዴራል ፖሊስን፤ የክልል ልዩ ኃይሎችንና የመደበኛ ፖሊስን ዩኒፎርሞች፣ የጸጥታ አካላት አባል ያልሆነ ማንኛውም ሰው ለብሶ መገኘት ፈጽሞ የተከለከለ ነው ያለ ሲሆን፣ የተቋማቱ አባል ሳይሆንና የታደሰ መታወቂያ ሳይዝ ዩኒፎርሙን ለብሶ በተገኘ ማንኛውም ሰው ላይ፣ የጸጥታ አካላት አስፈላጊውን ርምጃ እንዲወስዱ ትእዛዝ አስተላልፏል።
ማንኛውም ወታደራዊ እንቅስቃሴዎችን፣ የጦር ሜዳ ውሎዎችንና ውጤቶችን በተመለከተ፣ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ዕዝ ሥልጣን ከተሰጠው አካል ውጪ፣ በየትኛውም የመገናኛ አውታር መስጠትና ማሰራጨት ክልክል ነው። በየግንባሩ የሚገኙ የሲቪልና ወታደራዊ አመራሮች ከተሰጣቸው ሥምሪትና ተልእኮ ውጭ ማንኛውንም ወታደራዊ እንቅስቃሴዎችን፣ የጦር ሜዳ ውሎዎችንና ውጤቶችን የሚመለከቱ መግለጫዎች መስጠት የተከለከለ ነው። የጸጥታ አካላትም ይሄን ተላልለፈው በሚገኙት ላይ አስፈላጊውን ርምጃ እንዲወስዱ ታዟል።
እንዲሁም ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ ከሚፈቅደው ውጪ የሽግግር መንግሥት ወይም ሌላ ሕገ ወጥ ቅርጽ ያለው መንግሥት እንመሠርታለን ብለው ተግባራዊ እንቅስቃሴ በሚያደርጉ አካላት ላይ የጸጥታ አካላት አስፈላጊውን ርምጃ እንዲወስዱ ታዟል።
የሐሳብ ነጻነትን ሰበብ በማድረግ ልዩ ልዩ የሚዲያ አውታሮችን በመጠቀም፣ የሽብር ቡድኑን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ በመደገፍ በህልውና ዘመቻው ላይ ዕንቅፋት የሚፈጥሩ አካላት ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ የአስቸኳይ ጊዜ ዕዝ ያስጠነቀቀ ሲሆን፣ ይሄንን ማስጠንቀቂያ ተላልፈው ከድርጊታቸው በማይቆጠቡ አካላት ላይ የጸጥታ ኃይሎች ተገቢውን ርምጃ እንዲወስዱ ታዟል።