ፕሬዝዳንት መሀመድ ፋርማጆ እና የፑንትላንድ ፕሬዝዳንቱ አብዱላሂ ዴኒ በምርጫው ተጠባቂዎች ናቸው
ሶማሊያዊያን ከ10 ቀን በኋላ ፕሬዝዳንታቸውን ይመርጣሉ
16 ሚሊዮን ህዝብ ያላት ጎረቤት ሀገር ሶማሊያ ከ10 ቀን በኋላ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ እንደምታካሂድ ተገልጿል፡፡
ሶማሊያዊያን ፕሬዝዳንታቸውን በቀጥታ ባይመርጡም በተወካዮቻቸው አማካኝነት የሚመርጡ ሲሆን 300 የሚሆኑት የሶማሊያ የጎሳ ተወካዮች ቀጣዩን የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት እንደሚመርጡ ይጠበቃል፡፡
ሶማሊያዊያን 10ኛ ፕሬዝዳንታቸውን የሚመርጡበት ምርጫ ሳምንት እሁድ እንዲካሄድ የወሰነው በአዲስ መልክ የተቋቋመው የሃገሪቱ ምርጫ ኮሚሽን ነው፡፡
ከ2017 ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ በስልጣን ላይ ያሉት ፕሬዝዳንት መሀመድ ፋርማጆ የአስተዳድር ጊዜያቸው ከሁለት ዓመት በፊት የተጠናቀቀ ቢሆንም በኮሮና ቫይረስ እና በድርቅ ምክንያት ምርጫው ሳይካሄድ ቀርቷል፡፡
የሀገሪቱ እንደራሴዎች ምክር ቤት ለሁለት ዓመት ስልጣናቸው የተራዘመላቸው ፕሬዝዳንት ፋርማጆ ከአንድ ሳምንት በኋላ ለሁለተኛ ጊዜ የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ለመሆን ይወዳደራሉ፡፡
በዚህ ምርጫ ላይ ፕሬዝዳንት መሀመድ ፋርማጆ እና የፑንትላንድ ራስ ገዝ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ሰዒድ አብዱላሂ ዴኒ በምርጫው ተጠባቂዎች ናቸው፡፡ ምርጫውን ተከትሎ በሶማሊያ አለመረጋጋት እንዳይከሰት ተሰግቷል፡፡
የሶማሊያ ምርጫ ከሌሎች ሀገራት ለየት ባለ መንገድ የሚካሄድ ሲሆን 14 ሺህ የሚሆኑ የተለያዩ ጎሳ ተወካዮች 300 የእንደራሴ ምክር ቤት አባላትን ይመርጣሉ፡፡
የዚህ ምርጫ አካል የሆነው የተወካዮች ምክር ቤት አባላት ምርጫ በሶማሊያ ሁሉም ግዛቶች የሚካሄድ ሲሆን ሱማሊላንድ የ46 ተወካዮች ምርጫን ስታጠናቅቅ በቀሪዎቹ ማለትም በፑንትላንድ፣በደቡብ ምዕራብ ፣በጁባላንድ፣ በጋልሙዱግ፣ በሂርሻበሌ እና በናድር ግዛቶች እስካሁን የእንደራሴዎች ምክር ቤት ተወካዮች ምርጫ አልተጠናቀቀም፡፡
በሶማሊያ በሽብርተኝነት በሚንቀሳቀሰው አልሻባብ ይህ ምርጫ በሰላም እንዳይጠናቀቅ እና ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር እንዳይኖር እንቅፋት ሊፈጥር እንደሚችል ተሰግቷል፡፡
አል ሸባብ ከሰሞኑ በአፍሪካ ህብረት ሰላም አስከባሪ ጦር ላይ ጥቃት መፈጸሙ ይታወሳል፡፡
የሶማሊያ ምርጫ በመራዘሙ ምክንያት አሜሪካ እና የአውሮፓ ህብረት በሀገሪቱ አመራሮች ላይ ማዕቀብ የጣሉ ሲሆን ምርጫው አሁን ከተያዘለት ጊዜ እንዳይራዘምም አሳስበዋል፡፡