አሜሪካ አብዱላሂ ናድር ያለበትን ለጠቆመ ሶስት ሚሊዮን ዶላር እሰጣለሁ ብላ ነበር
ከአልሻባብ መስራቾች አንዱ የነበረው አብዱላሂ ናድር መገደሉን የሶማያ መንግስት አስታወቀ።
ጎረቤት ሀገር ሶማሊያ አልሻባብን ለማጥፋት መጠነ ሰፊ ጥቃት የከፈተች ሲሆን የሽብር ቡድኑ መስራች የነበረው አብዱላሂ ናድር መግደሏን አስታውቃለች።
የሶማሊያ መንግስት የጸጥታ ሀይል እየወሰደ ባለው ጥቃት ከዚህ በፊት በሽብር ቡድኑ ይዞታ ስር የነበሩ ቦታዎችን አስለቅቋል ተብሏል።
አኣሻባብም በተለይም የአጥፍቶ ማጥፋት ጥቃቱን የቀጠለ ሲሆን ባሳለፍነው ሳምንት ብቻ ባደረሳቸው ሁለት ጥቃቶች የ16 ሰዎች ህይወት አልፏል።
ከአልቃይዳ ጋር ግንኙነት እንዳለው የሚገለጸው አልሻባብ መስራች የነበረው አብዱላሂ ናድር ከዚህ በፊት የሽብር ቡድኑን ሲመራ የነበረው እና በቅርቡ የተገደለው አህመድ ድርዬን ለመተካት በሂደት ላይ እንደነበር ሮይተርስ ዘግቧል።
የሶማሊያ የኢንፎርሜሽን ሚንስቴር ባወጣው መግለጫ የአብዱላሂ ናድር መገደል አልሻባብ ከሶማሊያውያን ላይ እንደ እሾህ ተነቅሎ እንዲወጣ ያደርገዋል ብሏል።
ይህ የሽብር ቡድኑ አመራር እንዲገደል ሶማሊ ህዝብ እና ለዓለም አቀፍ ወዳጆች ላደረጉት ድጋፍ ምስጋናውን የሶማሊያ መንግስት አቅርቧል።
አልሻባብ ባለፉት 20 ዓመታት ውስጥ በ10 ሺህ የሚቆጠሩ ዜጎችን እንደገደለ የገለጸው የሶማሊያ መንግስት፤ ዓላማው ሶማሊያን እና ጎረቤት ሀገራትን ማወክ እንደነበርም ተገልጿል።
በቅርቡ በተካሄደ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ወደ ስልጣን የመጡት ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሀመድ አልሻባብን እንደሚያጠፉ ቃል ገብተው ነበር።
በቃላቸው መሰረትም ፕሬዝዳንቱ ከጎረቤት ሀገራት እና ከአሜሪካ ጋር በመቀናጀት የአልሻባብን ዋነኛ አመራሮች እንዲገደሉ አድርገዋል ተብሏል።
ይሁንና የአሁኑ የአልሻባብ የሽብር ቡድን መሪ የተገደለው በማን አጋዥነት እንደሆነ የሶማሊያ መንግስት ያለው ነገር የለም።
ኢትዮጵያ በተናጥል እና በአፍሪካ ህብረት ስር ካለው የሶማሊያ ሰላም ማስከበር ተልዕኮ ጦር ማዋጣቷ ይታወሳል።
የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሀመድ ባሳለፍነው ሳምንት በአዲስ አበባ ጉብኝት ያደረጉ ሲሆን ከጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ ጋር በብዙ ጉዳዮች ዙሪያ መምከራቸውን በጋራ ባወጡት መግለጫ ላይ ጠቁመዋል።