ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ለሁለተኛ ጊዜ በቱርክ ድርድር ሊያደርጉ መሆኑ ተነገረ
በሶማሊላንድ በኢትዮጵያ መካከል የተፈረመውን የወደብ ስምምነት ተከትሎ በሞቃዲሾ እና በአዲስ አበባ መካከል ዲፕሎማሲያዊ ውጥረት መፈጠሩ ይታወሳል
ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ የመጀመርያ ዙር ደርድራቸውን ባለፈው ወር ላይ በቱርክ አንካራ አድርገው ነበር
በኢትዮጵያ እና ሶማሊያ መካከል የሚደረገው ሁለተኛ ዙር ድርድር በሚቀጥለው ሳምንት በቱርክ አንካራ እንደሚካሄድ ተነገረ፡፡
የቱርክ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ሀከን ፊደን እንደተናገሩት ሀገራቱ ልዩነታቸውን በንግግር ለመፍታት በተስማሙት መሰረት ሁለተኛ ዙር ድርድራቸውን ያደርጋሉ ብለዋል፡፡
በዚህኛው ዙር ድርድር ሀገራቱ ከመጀመርያው ዙር በተሻለ ለመስማማት እንደሚቀራረቡ ተስፋ እናደርጋለን ያሉት የውጭ ጉዳይ ሚንስትሩ፣ ቱርክ ሁለቱ ወገኖች ከስምምነት እንዲደርሱ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቷን እንደምትቀጥል ነው ያስታወቁት፡፡
ከሰሞኑ በኢትዮጵያ ጉብኝት ያደረጉት የውጭ ጉዳይ ሚንስትሩ በአዲስ አበባ ቆይታቸው ከጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ ጋር በጉዳዩ ላይ እንደመከሩ እና በሶማሊያ ግዛታዊ አንድነት እና ሉአላዊነት ላይ ኢትዮጵያ ጥያቄ እንደሌላት እንዳረጋገጡላቸው ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ከቅርብ አመታት ወዲህ ከሶማሊያ ጋር ግንኙነቷን እያጠናከረች የምትገኝው ቱርክ ትምህርት ቤቶች፣ ሆስፒታሎች እና መሰረተ ልማቶችን ለሞቃዲሾ የገነባች ሲሆን በተጨማሪም ለበርካታ ሶማሊያውያን በቱርክ የነጻ ትምህርት እድል ሰጥታለች፡፡
ከዚህ ባለፈ በ2017 አንካራ ከድንበሯ ውጭ ግዙፍ የሚባለውን ወታደራዊ ካምፕ በሶማሊያ አቋቁማለች። በተያዘው አመት ደግሞ ሁለቱ ሀገራት የኢኮኖሚ እና ወታደራዊ ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡
በስምምነቱ መሰረት አንካራ የሶማሊያን የባህር ክልል ለመጠበቅ የባህር ሀይል ድጋፍ ለማድረግ ቃል ገብታለች፡፡
ባሳለፍነው ሳምንት ሶማሊላንድ የሀገርነት እውቅናን ለማግኘት የምታደርገውን ጥረት የሚያስፈጽም ግብረ ሀይል በሚንስቴር ደረጃ ማቋቋሟን ማስታወቋ አይዘነጋም፡፡
ራስ ገዟ ሶማሊላንድ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሯ በኩል ባወጣችው መግለጫ የግብረ ሀይሉ መቋቋም ሀገር ለመሆን ለሚደረገው ጥረት ወሳኝ እርምጃ ነው ብላለች፡፡
ግብረ ሀይሉ እውቅና ለማግኘት የሚደረጉ ጥረቶችን በስትራቴጃዊ ጉዳዮች በመደገፍ ሂደቱን ለማፋጠን ይሰራል ተብሏል፡፡
በተጨማሪም ከኢትዮጵያ ጋር በተደረሰው የመግባብያ ስምምነት መሰረት ሂደቱ የሚፋጠንበትን እና ወደ ተግባር በሚለወጥበት ሁኔታ ላይ አተኩሮ እንደሚሰራ አስታውቋል፡፡
ከወራት በፊት ኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ በተፈራረሙት የመግባብያ ስምምነት ኢትዮጵያ በኤደን ባህረ ሰላጤ ለ50 አመታት በሊዝ ኪራይ የሚቆይ 20 ኪሎሜትሮች የሚረዝም የባህር ጠረፍ እንድታገኝ እና በምላሹ አዲስ አበባ ለሶማሊላንድ እውቅና እንድትሰጥ ስምምነት ላይ መድረሳቸውን አስታውቀው ነበር፡፡
ይህን ተከትሎም በሶማሊያ እና በኢትዮጵያ መካከል ዲፕሎማሲያዊ ውጥረት መፈጠሩ አይዘነጋም።
ተመድን ጨምሮ የተለያዩ ባለብዙ ወገን ድርጅቶች እና ሀገራት በሶማሊያ እና በኢትዮጵያ መካከል በወደብ ስምምነቱ ምክንያት የተፈጠረው ውጥረት ወደ ግጭት እንዳያመራ ሲያስጠነቅቁ ሰንብተዋል።