“ከአመራር ለውጡ በኋላ ያጋጠሙ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችል ሥልጣን አልነበረኝም”- ጠ/ሚ ዐቢይ
የቀድሞው የደህንነት ሹም አቶ ጌታቸው አሰፋ ትልቅ እንቅፋት ሆነውባቸው እንደነበርም ገልጸዋል
“በሱማሌ ክልል ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሲጠነሰስ ነበር”ም ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያሉት
“ከአመራር ለውጡ በኋላ ያጋጠሙ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችል ሥልጣን አልነበረኝም”- ጠ/ሚ ዐቢይ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የሀገሪቱ ርዕሰ መስተዳድር ሆነው ከተሾሙ በኋላ በሀገሪቱ ያጋጠሙ ችግሮችን ወዲያውኑ ለማስቆም የሚያስችል ስልጣን እንዳልነበራቸው አስታወቁ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከአመራር ለውጡ ወዲህ ጀምሮ ያሉ ሁነቶችን ለምክር ቤት አባላት አብራርተዋል፡፡
ወደ ኃላፊነት በመጡበት ወቅት የህወሃትን ጥፋት ለምን አላስቆሙም?፣ የሕግ ማስከበር ዘመቻውስ ቶሎ ለምን አልተጀመረም ነበር? የሚሉ ጥያቄዎች የቀረቡላቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ቢሮ ከገቡ ጀምሮ በመኖሪያ ቤታቸውም ሆነ በቢሯቸው ውስን እንቅስቃሴ እንዲያደርጉ ይነገራቸው እንደነበር አንስተዋል፡፡
በዚህም የተነሳ መስራት ያሉባቸውን ስራዎች በሙሉ መስራት ሳይችሉ መቅረታቸውንም ገልጸዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እንዳሉት እርሳቸው ወደ ኃላፊነት ከመጡበት ዕለት ጀምሮ ከፍተኛ ፈተና ገጥሟቸው ነበር፡፡
የቀድሞው የደህንነት ሹም አቶ ጌታቸው አሰፋ ትልቅ የሥራ እንቅፋት ሆነው እንደነበር የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሹሙ ተባብሮ ለመስራት ፍላጎት እንዳልነበራቸው አንስተዋል፡፡
በወቅቱ ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን እና ከሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች ጋር በመነጋገር“ለውጡ እንዳይቀለበስ እና ህዝቡም እንዲረዳ ለማድረግ ሞክረን ነበር”ም ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡
“በሱማሌ ክልል ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሲጠነሰስ ነበር”ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቅድሚያ ወደ ስፍራው ጉብኝት ማድረጋቸውን አስታውሰዋል፡፡
“የደህንነት ሹሙ ወደ ሱማሌ መሄድ እንዳልችል አድርጎኝ ነበር”ያሉም ሲሆን ክልከላው ወደ አምቦ፣ መቀሌና ጎንደር የተደረጉትን ጉብኝቶች እንደሚያካትትም ገልጸዋል፡፡
አቶ ጌታቸው ከኃላፊነት በተነሱ ማግስት በውል ያልታወቁ ዘመናዊ መሳሪያዎችን ይዘው ወደ ትግራይ ሄደዋል እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለጻ፡፡
መሳሪያዎቹ የሀገር ሀብቶች መሆናቸውን ተከትሎ እንዲመለሱ ለክልሉ ጥያቄ ቀርቦ ነበር፤ ሆኖም አልተሳካም፡፡ ብሄራዊው የደህንነት ተቋም ጭምር ከእውቀት ይልቅ በዘመድ አዝማድ በተሰባሰቡ ሰዎች የተሞላ ነው፡፡
በአጠቃላይ “ህወሃት በሀገሪቱ ግጭቶች እንዲከሰቱ በሰው ኃይልና በገንዘብ በመደገፍ ሀገር ለማተራመስ ሲሰራ ነበር” ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፡፡
በዚህም ከትግራይ ክልል ውጭ በሁሉም የሃገሪቱ አካባቢዎች በአጠቃይ 113 ግጭቶች በቅንብር እንዲከሰቱ መደረጋቸውን ገልጸዋል፡፡
በመከላከያ ሰራዊት ውስጥ ጭምር የአንድ ብሄር በዋናነትም የትግራይ ብሄር የረዥም ጊዜ የበላይነት እንደነበርም ገልጸዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡
በወታደራዊ አመራሮች መካከል ያለውን ልዩነት በቁጥር አስደግፈውም ነው ያስቀመጡት፡፡
በዚህም መሰረት 60 በመቶው ሙሉ ጄነራል፣ 50 በመቶው ሌፍተናንት ጄነራል፣45 በመቶ ሜጀር ጄነራል፣ 40 በመቶው ብርጋዴር ጄነራል፣ 58 በመቶው ኮሎኔል፣ 66 በመቶው ሌተናል ኮሎኔል፣50 በመቶው ሻለቃ በአጠቃላይ በአማካይ 55 በመቶ ያህሉ የሰራዊቱ ከፍተኛ መሪዎች ትግሬ እንደነበሩ ተናግረዋል፡፡
በስልጣን ደረጃም ቢሆን በመከላከያ ዋና መምሪያ 80 በመቶው በትግራይ ሰዎች መያዙን አንስተው በዕዝ ደረጃም አዛዥ እና ምክትል አዛዥ 100 በመቶ ከትግራይ የተውጣጣ ነበር ብለዋል፡፡
ይህ በራሱ ከባድ ፈተና እንዳስከተለ አንስተው በመከላከያ ላይ ማሻሻያዎችና ማስተካከያዎችን ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል፡፡