የደቡብ ምዕራብ ሶማሊያ ግዛት የፍትህ ሚኒስትር በአጥፍቶ ጠፊዎች መገደላቸው ተገለጸ
ሚኒስትሩን ለመግደል በተወረወረው የቦንድ ፍንዳታ ሌሎች 10 ሰዎች ቆስለዋል
የሰማሊያ ፌዴራል መንግስትም ሆነ የግዛቱ አስተዳደር በጉዳዩ ላይ እስካሁን ያሉት ነገር የለም
የደቡብ ምዕራብ ሶማሊያ ግዛት የፍትህ ሚኒስትር ሼክ ሃሰን ኢብራሂም ሉግቡር በአጥፍቶ ጠፊዎች መገደላቸው ተገለጸ፡፡
የፍትህ ሚኒሰትሩ ሼክ ሃሰን ኢብራሂም ሉግቡር ተገደሉት ከሞቃዲሾ በ245 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በባይዶዋ በሚገኘው መስጂድ የጁምአ ሰላት ሰግደው በመውጣት ላይ ሳሉ በአጥፍቶ ጠፊዎች በተሰነዘረባቸው ጥቃት መሆኑም የሀገሪቱ የመንግስት ሚዲያ ዘግቧል፡፡
በፍንዳታው ሌሎች 10 ሰዎች መቁሰላቸውንም ነው የተገለጸው፡፡
የደቡብ ምዕራብ ሶማሊያ የፍትህ ሚኒስቴር ባወጣው የሃዘን መግለጫ፤ በሚኒስትሩ ድንገተኛ ህልፈት እጅጉን ማዘኑን ገልጿል፡፡
ሚኒስትሩ የህዝቦችን ህይወት ላማሻሸል ሌት ተቀን ደፋ ቀና ሲሉ የነበሩ አገልጋይና ባለራዕይ መሪ ነበሩም ብለዋል መግለጫ።
የሰማሊያ ፌዴራል መንግስትም ሆነ የግዛቱ መንግስት በጉዳዩ ላይ እስካሁን ያሉት ነገር የለም፡፡
ለጥቃቱ ሃላፊነቱን የወሰደ አካል ባይኖርም ጣቶች በማነጣጠር ላይ ያሉት ግን አብዛኛውን ጊዜ መሰል ድርጊቶችን ወደ ሚፈጽመው አሸባሪው አልሸባብ ነው ተብሏል፡፡
የደቡብ ምዕራብ ሶማሊያ፣ በደቡብ ምዕራብ ሶማሊያ የሚገኝ የፌዴራል አባል ግዛት ነው።
ግዛቱ እንደፈረንጆቹ ሚያዝያ 1 ቀን 2002 በሶማሊያ መሪ ሃሰን ሙሀመድ ኑር ሻቲጋዱድ አባካኝነት ሶስተኛው ራስ ገዝ ክልል ሆኖ እንደተመሰረተም ይታወቃል፡