ፋርማጆ በጉጉት በሚጠበቀው የሶማሊያ ምርጫ ለ2ኛ ጊዜ እጩ መሆናቸውን አስታወቁ
ፎዚያ ዩሱፍ በምርጫው ለመወዳደር የተመዘገቡ ብቸኛዋ እጩ ሆነው ቀርበዋል
"የሶማሊያ ህዝብ ባቀረበው ጥሪ መሰረት በድጋሚ ለፕሬዝዳንትነት ለመወዳደር ወስኛለሁ" ብለዋል ፕሬዝዳንት ሞሃመድ አብዱላሂ
የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሞሃመድ አብዱላሂ ሞሃመድ (ፋርማጆ) በጉጉት በሚጠበቀው የሀገሪቱ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ለሁለተኛ ጊዜ እጩ መሆናቸውን አስታውቋል።
ፋርማጆ፤ ለሁለተኛ ጊዜ የፕሬዝዳንትነት ስልጣን የሚፈልጉት ሶማሊያ በስልጣን ዘመናቸው ያስመዘገበችውን "የተሳካ" ለውጥ ለማስቀጠል እንደሆነም በትዊተር ገጻቸው ባጋሩት አጭር ቪዲዮ ገልጸዋል፡፡
"በጀመርነው የእድገት ጎዳና ለመቀጠል ቁርጠኛ ሆኜያለሁ፤ የሶማሊያ ህዝብ የሚወክለውና ፍላጎቶቹን የሚያሟላለት መንግስት ይገባዋል፤ ለዚህም ነው የሀገራችንን ስኬትና ለውጥ ለማስቀጠል ለሁለተኛ ጊዜ ፕሬዝዳንት መሆን የምፈልገው” ሲሉ በድጋሚ እጩ ሆኖ ለመቅረብ ስላበቃቸው ምክንያት ገልጸዋል ፋርማጆ።
የጁባ ላንድ ክልል ፕሬዝዳንት የሆኑት አህመድ ሼክ መሃመድ ኢስላም (ማዶቤ)ን ጨምሮ ሌሎች የሃገሪቱ ፖለቲከኞች በምርጫው ብርቱ ፉክክርን እንደሚያደርጉ ይጠበቃል፡፡
ፎዚያ ዩሱፍ በምርጫው ለመወዳደር የተመዘገቡ ብቸኛዋ ሴት እጩ ሆነው ዛሬ ሰኞ መቅረባቸውንም የሃገሪቱ ሚዲያዎች ዘግበዋል፡፡
የቀድሞውን የሃገሪቱን ፕሬዝዳንት ሃሰን መሃሙድን ጨምሮ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ሃሰን ካይሬ እጩ ሆነው መቅረባቸውም ተነግሯል፡፡ እስካሁን በድምሩ ከ10 በላይ ተወዳዳሪዎች በእጩነት መመዝገባቸውንም ነው የሃገሪቱ ምርጫ ኮሚሽን ያስታወቀው፡፡
የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከግድያ ሙከራ ተረፉ
ምርጫው የሚካሄደው የሶማሊያ ወጣቶች ሊግ 79ኛ ዓመት የምስረታ በዓል በሚከበርበት ዕለት በመጪው እሁድ ግንቦት 7 ቀን 2014 ዓ/ም (በፈረንጆቹ ግንቦት 15) ነው፡፡
የዕለቱን ታሪካዊነት ያነሱት ፋርማጆ የሶማሊያ ወጣቶች ለሃገራቸው ነፃነት ባደረጉት ትግል የከፈሉትን መስዋዕትነት በማስታወስ የሶማሊያውያንን ብሄራዊ ኩራት ለመመለስ ቁርጠኛ መሆናቸው መልእክት አስተላልፈዋል፡፡
"የሶማሊያ ህዝብ ባቀረበው ጥሪ መሰረት በድጋሚ ለፕሬዝዳንትነት ለመወዳደር ወስኛለሁ" ሲሉም ተደምጠዋል ፕሬዝዳንቱ።
ይሁን እንጂ አጭር የነበረው የፕሬዝዳንቱ ንግግር ፋርማጆ የሶማሊያውያንን ህይወት ለመቀየር ስላስቀመጡት ቀጣይ ስትራቴጂ ግልጽ ያላደረገ ነው የሚል ትችት አስከትሏል፡፡
በሶማሊያ ህገ-መንግስት መሰረት የሞሃመድ አብዱላሂ ሞሃመድ /ፋርማጆ/ ስልጣን ያበቃው እንደፈረንጆቹ በየካቲት 8፣ 2021 ነበር።
የፋርማጆ ስልጣን የማራዘም ፍላጎት እና የሶማሊያ መሪዎች አለመስማማት ሀገሪቱን ለከፍተኛ የፖለቲካ ውጥረት ዳርጓት እንደቆየም የሚታወቅ ነው፡፡
ሶማሊያውያን ከቀናት በኋላ የሚያካሂዱት ምርጫ በመስቀለኛ መንገድ ላይ ያለቸውን ሀገር ቀጣይ እጣ ፈንታ የሚወስን ነው ተብሎለታል፡፡