በሶማሊያ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ሰይድ አብዱላሂ ዴኒ እየመሩ ነው
የሶማሊያ ፓርላማ እያካሄደ ባለው ምርጫ 39 ሰዎች ለፕሬዝዳንትነት ለመወዳደር በእጩነት ቀርበዋል
በመጀመሪያ ዙር ምርጫ ሰይድ አብዱላሂ ዴኒ በ65 ደምጽ እየመሩ ሲሆን፤ ፐሬዝዳንት መሃመድ አብዱላሂ ፋርማጆ በ61 ይከተላሉ
ሶማሊያ በተለያዩ ምክንያች ለሁለት ዓመት የተራዘመውን የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ምርጫ በዛሬው እለት በማካሄድ ላይ ይገኛል።
የሀገሪቱ ፓርላማ በፀጥታ ስጋት በሀጋር አውሮፕላን ማረፊያ ውስጥ እያካሄደ ባለው ምርጫ እስካሁን የመጀመሪያ ዙር ውጤት ታውቋል።
በዚህም ሰይድ አብዱላሂ ዴኒ በ65 ደምጽ እየመሩ ሲሆን፤ ፕሬዝዳንት መሃመድ አብዱላሂ ፋርማጆ በ61 ድምጽ በሁለተኝነት እየተከተሉ መሆኑን ሲ.ጂ.ቲ.ኤን ዘግቧል።
ሀሰን ሼክ መሃመድ 52 ድምጽ እንዲሁም ሀሰን አሊ ካሂሬ 48 ድምጽ በማግኘት ለሁለተኛ ዙር ምርጫ ማለፋቸው ተነግሯል
እየተካሄደ ባለው ምርጫ ላይ ለመወዳደር በስልጣን ላይ ያሉትን መሃመድ አብዱላሂ መሃመድ ፋርማጆን ጨምሮ 39 ሰዎች ለፕሬዝዳንትነት ለመወዳደር በእጩነት ቀርበዋል።
ከዚህ ቀደም የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው ያገለገሉት ፋውዚያ የሱፍ ሀጂ አደም ብቸኛ ሴት እጩ ሲሆኑ፤ ሁለት የቀድሞ ፕሬዝዳንቶችም በእጩነት መቅረባቸው ተሰምቷል።
የሶማያ ፕሬዚዳንት ምርጫ በከፍተኛ የፀጥታ ስጋት ውስጥ እየተካሄደ ሲሆን፤ ስጋቱም ከአልቃይዳ ጋር ግንኙነት ያለው የታጣቂ ቡድን አልሸባብ በሞቃዲሾ እና በአፍሪካ ቀንድ ሀገራት ተከታታይ ጥቃቶችን እየፈፀመ ያለበት ወቅት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ እንደሆነም ተነግሯል።
የሶማሊያ ፖሊስ ቃል አቀባይ አብዲፈታህ አደን በትናትናው እለት በሰጡት መግለጫ፤ ሞቃዲሾ ከተማ ለ33 ሰዓታት ማለትም ከትናንት ምሽት 3 ሰዓት እስከ ነገ ጠዋት 12 ሰዓት ድረስ የትራፊክ እና ሰዎች እንቅስቃሴ ላይ ክልከላ መጣሉን አስታውቀዋል።
ፕሬዝዳናታዊ ምርጫውም በሀጋር አውሮፕላን ማረፊያ ውስጥ እየተካሄደ ሲሆን፤ ይህም ሊፈፀም የሚችል የሽበር ጥቃትን ለመከላል በሚያስችል ስፍራ ነው ተብሏል።
ከ2017 ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ በስልጣን ላይ ያሉት ፕሬዝዳንት መሀመድ ፋርማጆ የአስተዳድር ጊዜያቸው ከሁለት ዓመት በፊት የተጠናቀቀ ቢሆንም በኮሮና ቫይረስ እና በድርቅ ምክንያት ምርጫው ሳይካሄድ ቀርቷል፡፡