ፕሬዝደንት ሀሰን ሼህ መሀመድ ፕሬዝደንት ፈርማጆን በመተከት ነው በቅርቡ ፕሬዝደንት ሆነው የተመረጡት
የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ መሐመድ ሀገራቸው የምስራቅ አፍሪካ የጋራ ገበያን መቀላቀል እንደምትፈልግ አረጋገጡ።
ፕሬዝዳንቱ ይህንን ያሉት በታንዛኒያ በተዘጋጀው የጋራ ገበያው ስብሰባ ላይ መሆኑ ተገልጿል።
ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ መሐመድ የምስራቅ አፍሪካ የጋራ ገበያ አባል ሀገራት ለሶማሊያ ላደረጉት ድጋፍ ምስጋና ማቅረባቸውንም ጽ/ቤታቸው አስታውቋል።ሀገራቱ ለሶማሊያ ሰላምና መረጋጋት ወታደር በመላክ ጭምር አጋርነታቸውን በማሳየታቸውም ፕሬዝዳንቱ አመስግነዋቸዋል።
ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ መሐመድ የጋራ ገበያውን ስብሰባ የተከታተሉት ትናንትና ምሽት ሲሆን ዋና ጸሐፊው ፔተር ሙቱኩ ማቱኪ አቀባበል አድርገውላቸው ነበር።
ፕሬዝዳንቱ የምሽቱ የጋራ ገበያው አባል ሀገራት ስብሰባ ላይ ልዩ እንግዳም ነበሩ።
በአሩሻ ከተማ በተካሄደው 22 ኛው የምስራቅ አፍሪካ የጋራ ገበያ አባል ሀገራት ጉባዔ ላይ ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ መሐመድ የሶማሊያን የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ የሀብት ዕድሎችን ጠቅሰዋል ተብሏል።
የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት የማደግ ዕጣ የተያያዘ እንደሆነም ነው የሶማሊያው ፕሬዝዳንት በመድረኩ የተናገሩት።
ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ መሐመድ የመንግስታቸው የመጀመሪያ ትኩረት ሰላምና መረጋጋት ማረጋገጥ መሆኑን መግለጻቸው ይታወሳል።