አንዳንድ ወገኖች “ከአሸባሪ ቡድን ጋር ድርድር” ታስቧል የሚሉት “ስህተት ነው”-መንግስት
ህወሓት በአንጻሩ “ለሰላም እድል ለመስጠት” ሲባል ከአማራ እና አፋር ክልሎች ተዋጊዎቹን ማስወጣቱን ገልጿል
መንግስት ሊደረግ የታሰበው ሀገራዊ ምክክር ቀደም ተብሎ የተጀመረ መሆኑን እና ከጦርነቱ ጋር እንደማይገናኝ አስታውቋል
የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ዛሬ በሰጠው መግለጫ ኢትዮጵያ ልታካሂድ ያሰበችውን ሀገራዊ ምክክር አላማ ወደ ጎን በመተው አንዳንዶች “ከአሸባሪ ቡድን ጋር ድርድር” እንደታሰበ አድርገው ማቅረባቸው ስህተት መሆኑን አስታውቋል፡፡
መንግስት ሀገረመንግስቱን አደጋ ላይ በሚጥል ተግባር ላይ ተንቀሳቅሰዋል በሚል ከወራት በፊት ህወሓት እና ሸኔ በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት በአሸባሪነት ማስፈረጁ ይታወሳል፡፡
የአገልግሎቱ ሚኒስትር ዴኤታ ከበደ ዴሲሳ እንደገለጹት ሊደረግ የታሰበው ሀገራዊ ምክክር ቀደም ተብሎ የተጀመረ መሆኑን አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ካለው ጦርነት ጋር አይገናኝም፡፡
ሚኒስትሩ ሀገራዊ ምክክሩ ከጦርነቱ ጋር በተያይዞ ከተወሰነ ቡድን ወይንም ግለሰብ ጋር የሚደረግ ድርድር አይደለም ብለዋል፡፡
የሀገረመንግስት ግንባት በሚያጠናክሩ ጉዳዮች ላይ ምክክር እንደሚያስፈልግ ጽኑ እምነት ያለው መንግሰት የምክክር ኮሚሽን ማቋቋሙን የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታው የሀገራዊ ምክክር አዋጅ በአጭር ጊዜ እንደሚጸድቅ ገልጸዋል፡፡
መንግስት ምክክሩን ለማካሄድ ነጻና ገለልተኛ ተቋም ማስፈለጉንና ምክክርና ድርድር በምን ጉዳይ ከማን ጋር ይደረጉ የሚለውን ያስተባብራል ብሏል ሚኒስትሩ፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴአታ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴንም ምክክሩ ከህወሃት እና ከሽኔ ጋር አይገኛኝም ብለዋል፡፡
“አንዳንድ ሰዎች ሁሉን አቀፍ ውይይትንና ድርድርን አደበላልቀውት ሲቸገሩ ይታያል። ውይይቱ ከአመት በፊትም የነበረና አሁን ግን ራሱን በቻለ ኮሚሽን ተጠናክሮ ይቀጥል ነው። ስለ ህወሓት ወይም ሸኔ አይደለም። ይህኛው የራሱ ሌላ መልክ አለው።”
ትግራይ ክልልን ሲያስተዳድር የነበረው ህወሓት በሰሜን እዝ ላይ ጥቃት መሰንዘሩን ተከትሎ የተቀሰቀሰው ጦርነት ባለፈው ጥቅምት 24 አንድ አመት አስቆጥሯል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት በወሰደው የህግ ማስከበር ዘመቻ የትግራይን ዋና ከተማ መቀሌን ጨምሮ በርካታ ቦታዎች መቆጣጠር ቢችልም ከ8 ወራት በኋላ የተናጠል ተኩስ አቁም አውጆ ጦሩን በትግራይ ማስወጣቱ ይታወሳል፡፡
መንግስት ይህን ቢልም፤ ህወሓት የመንግስት ጦር እንዲወጣ ማድረጉን በወቅቱ ገልጾ ነበር፡፡ህወሓት ትግራይን ከተቆጣጠረ በኋላ ወደ አማራና አፋር ክልል በመግባት በርካታ ቦታዎች መቆጣጠርም ችሎ ነበር፡፡
የኢትዮጵያ መንግሰት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ካውጀና ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ወደ ግንባር ከዘመቱ በኋላ በህወሃት ተይዘው የነበሩ በርካታ የአማራ እና የአፋር ክልል ቦታዎች ነጻ ወጥተዋል፡፡ መንግስት የህወሓት ሀይሎችን በማሸነፍ ይዘዋቸው ከነበሩ ቦታዎች እንዲወጡ ማድረጉን ሲገልጽ ህወሓት በአንጻሩ “ለሰላም እድል ለመስጠት” ሲባል ከአማራ እና አፋር ክልሎች ተዋጊዎቹን ማስወጣቱን ይገልጻል፡፡
ከአንድ አመት በላይ ያስቆጠረው ጦርነቱ በሺዎች ሲገደሉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ደግሞ ከቀያቸው ተፈናቅለው ህይወታቸው ተመሰቃቅሏል፡፡