የኦሚክሮን ስርጭት እየጨመረ መምጣቱን ተከትሎ ሆስፒታሎቿን ዝግጁ ማድረጓን ደቡብ አፍሪካ አስታወቀች
ብሔራዊ የኮሮና ግበረኃይልን ለአስቸኳይ ስብሰባ እንደሚጠሩም ነው ፕሬዝዳንት ራማፎዛ ያስታወቁት
በተለያዩ የሃገሪቱ ግዛቶች በኦሚክሮን የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎዛ አስታውቀዋል
የኦሚክሮን ቫይረስ ስርጭት እየጨመረ መምጣቱን ተከትሎ ሆስፒታሎቿን ዝግጁ ማድረጓን ደቡብ አፍሪካ አስታወቀች፡፡
ለአራተኛ ጊዜ ወደ ወረርሽኙ ማዕበል እየገባን ነው ያሉት የሃገሪቱ ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎዛ ወረርሽኙ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን ያላየናቸው የኢንፌክሽኖች መጠን እያጋጠመን ነው ብለዋል የወረርሽኙን ሁኔታ አስመልክተው በጻፉት ሳምንታዊ መልዕክት።
የደቡብ አፍሪካ ሳይንቲስቶች አዲስ የኮሮና ቫይረስ ዝርያ ማግኘታቸውን ካስታወቁበት ከዛሬ ሁለት ሳምንት ወዲህ ዝርያው በብዙ የሃገሪቱ ግዛቶች ተሰራጭቶ ይገኛል ብለዋል፡፡
እንደ ፕሬዝዳንቱ ገለጻ ከባለፈው ሳምንት ጀምሮ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች እለታዊ ቁጥር በአምስት እጥፍ ጨምሯል፡፡
ጉቴሬዝ ከ‘ኦሚክሮን’ጋር በተያያዘ የተጣሉ የጉዞ እገዳዎችን ‘አፓርታይድ’ ሲሉ ኮነኑ
ከሁለት ሳምንት በፊት ከሚመረመሩ ናሙናዎች በሁለት በመቶ ያህሉ ብቻ ነበር ቫይረሱ የሚገኘው፡፡ አሁን ግን ወደ 25 በመቶ ከፍ ብሏል፡፡
በመሆኑም ሆስፒታሎች ታማሚዎችን ለመቀበል የሚያስችል ዝግጅት ማድረጋቸውን ነው ያስታወቁት፡፡
ደቡብ አፍሪካውያን የቫይረሱን ክትባቶች እንዲወስዱና የጥንቃቄ መንገዶችን ያለ ምንም መዘናጋት እንዲተገብሩም አሳስበዋል፡፡
ራማፎዛ ብሔራዊ የኮሮና ቫይረስ ግብረ ኃይሉን ለአስቸኳይ ስብሰባ እንደሚጠሩም በመልዕክታቸው ገልጸዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት 83 ሺ ሰዎች በኮሮና ቫይረስ ተይዘው በሚገኙባት በደቡብ አፍሪካ ባለፉት 24 ሰዓታት 11 ሺ 125 ሰዎች በኮሮና ቫይረስ መያዛቸው በምርመራ ተረጋግጧል፡፡
ይህ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በ23.8 በመቶ መጨመሩን የሚያሳይ ነው እንደ ሃገሪቱ የተላላፊ በሽታዎች ኢንስቲትዩት ገለጻ፡፡
በወረርሽኙ ማዕከልነት በሚጠቀሰው ጓተንግ በተባለ የሃገሪቱ ግዛት ብቻ ባለፉት 24 ሰዓታት 8 ሺ ሰዎች መያዛቸው ተረጋግጧል፡፡
የኦሚክሮን መገኘትን ተከትሎ የተለያዩ ሃገራት የጉዞ እገዳዎችን መጣላቸው ይታወሳል ምንም እንኳን እገዳውን ደቡብ አፍሪካን ጨምሮ የአፍሪካ ህብረትን መሰል አህጉራዊ ተቋማት ቢቃወሙትም፡፡