የአሜሪካው ከፍተኛ ዲፕሎማት ማይክ ሐመር ኢትዮጵያን ጨምሮ ወደ ሶስት የአፍሪካ ሀገራት ጉዞ ጀመሩ
ልዩ መልዕክተኛው በጉዞዋቸው ከሀገራቱ ባላስልጣናት፣ አፍሪካ ህብረትና ዓለም አቀፍ ተቋማት ተወካዮች ጋር የሚገኛኙ ይሆናል
ማይክ ሐመር በቅረቡ በሰጡት መግለጫ የሰሜን ኢትዮጵያ ጉዳይ አሳሳቢ ቢሆንም “የድርድር ተስፋ አለ” ማለታቸው አይዘነጋም
በሰሜን ኢትዮጵያ የተከሰተው ጦርነት በድርድር እንዲፈታ ጥረት በማድረግ ላይ የሚገኙት የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልእክተኛ ማይክ ሐመር ወደ ናይሮቢ፣ ፕሪቶሪያ እና አዲስ አበባ ጉዞ ጀመሩ።
ማይክ ሐመር ከሰኞ መስከረም 23 አስከ ጥቅምት 08/2015 ዓ.ም ድረስ በሶስቱም ሀገራት በሚኖራቸው ቆይታ እንደገና ያገረሸው የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት አብቅቶ ድርድር መጀመር በሚቻልበት ሁኔታ እንደሚወያዩም ነው የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ያስታወቀው።
ሐመር በናይሮቢ ቆይታቸው ከኬንያ መንግስት ባለስልጣናት፣ ዓለም አቀፍ አጋሮች፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እና ሌሎች ሰላምን ለመፍጠር እና ሰብአዊ እርዳታን ለተቸገሩ ወገኖች ለማድረስ በቀጠናዊ ጥረቶች ላይ ከሚሳተፉት ጋር አካላት ጋር ተገናኝተው በኢትዮጵያ ሰላም ጉዳይ ይመክራሉም ብሏል መግለጫው።
ልዩ መልዕክተኛው በፕሪቶሪያ ከደቡብ አፍሪካ መንግስት ባለስልጣናት ጋር በመገናኘት በኢትዮጵያ ያለውን ሁኔታ እንዲለወጥ በአፍሪካ ህብረት ጥላ ስር መደረግ ባለባቸው የጋራ ጥረቶች ላይ እንደሚወያዩም ተገልጿል።
በተጨማሪም ማይክ ሐመር ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ ከኢትዮጵያ መንግስት፣ ከአፍሪካ ህብረት ባለስልጣናት እንዲሁም በድርቅ ለተጎዱ አካባቢዎች እርዳታ በማቅረብ ላየ ከሚገኙ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ባለስልጣናት እና ሌሎች አጋሮች ጋር የሚገኛኙ ይሆናል።
ልዩ መልእክተኛው ማይክ ሐመር ባለፈው ነሃሴ ድጋሚ የተቀሰቀሰውን ጦርነት ለማስቆም እና ድርድር እንዲጀመር ለማበረታታት አዲስ አበባ ሰንብተው ከሳምነታት በፊት ወደ ዋሽንግተን መመለሳቸው የሚታወስ ነው።
ማይክ ሐመርወደ አሜሪካ ከተመለሱ በኋላ በሰጡት ማብራሪያ፤ ህወሓት እና በፌደራል መንግስት መካከል ያለውን ግጭት ለማስቆም ዋነኛ እንቅፋት የሆነው “በሁለቱም ወገኖች በኩል ያለው አለመተማመን ነው” ማለታቸው አይዘነጋም።
ጉዳዩ አሳሳቢ ቢሆንም ግን “የድርድር ተስፋ አለ”ም ነበር ያሉት ማይክ ሐመር።
ሁለቱም ወገኖች የጦርነት አማራጭን ትተው በጠረጴዛ ዙሪያ ለመቀመጥ የሚያስችል “ደፋር ውሳኔ እንደሚወስኑ ተስፋ አለን”ም ብለዋል ልዩ መልእክተኛው።
ከተጀመረ ሁለት ዓመት የሞላው የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ለወራት ቆሞ የነበረ ሲሆን፣ ባለፈው ነሐሴ 18/2014 ዓ.ም ድጋሚ መቀስቀሱ ይታወሳል።
ጦርነቱን እንደ አዲስ በመጀመር መንግስት እና ህወሓት እርስ በእርስ ሲካሰሱ ይስተዋላል። ያም ሆኖ ሁለቱም አካላት የተደጀመረውን ሰላም ንግግር ጥረት እንዲቀጥል ዝግጁ መሆናቸው ሲገልጹ ይደመጣሉ።
የኢትዮጵያ መንግስት በድጋሚ ጦርነት ከመቀስቀሱ በፊት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በየትኛው ቦታ በአፍሪካ ህብረት ጥላ ስር ከህወሓት ጋር እንደሚደራደር መግለጹ ይታወሳል።
አፍሪካ ህብረት “ሰላም ሊያመጣ አይችልም” አስከማለት ደርሶ ነበረው ህወሓትም ቢሆን፤ በአፍሪካ ህብረት ጥላ ስር በሚካሄደው የሰላም ድርድር ሂደት ውስጥ ለመሳተፍ ዝግጁ መሆኑ በቅርቡ ባወጣው መግለጫ ማስታወቁም ይታወሳል።